ቻይና በአፍሪካ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ፖለቲካዊ አንድምታ እንደሌለው ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ ገለፁ

ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ለአፍሪካ ብልጽግና የሚውል ተጨማሪ 60 ቢሊየን ዶላር ለመመደብም ለማድረግ ቃል ገብተዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ለአፍሪካ ብልጽግና የሚውል ተጨማሪ 60 ቢሊየን ዶላር ለመመደብም ለማድረግ ቃል ገብተዋል

የቻይናው ፕሬዘዳንት ሺ ዢፒንግ ቻይና ለአፍሪካ ቀጣይ ልማት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ገንዘብ እያፈሰሰች መሆኑን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን የተናገሩት ቻይና በአፍሪካ ውስጥ "የታይታ ፕሮጀክት" የላትም ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

ፕሬዚዳንቱ የቻይና-አፍሪካን ጉባኤን በቤጂንግ ሲከፍቱ፤ ለአፍሪካ ብልጽግና የሚውል ተጨማሪ 60 ቢሊየን ዶላር ለመመደብም ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ገንዘቡ በእርዳታና በብድር መልክም ለአህጉሪቱ የሚሰጥ ይሆናል።

በጉባኤው ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድን ጨምሮ፣ ከኢስዋቲኒ በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

ቻይና ለአፍሪካ መሰረተ ልማት ግንባታ የገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ቀዳሚዋ ሀገር ናት።

ተቺዎች በበኩላቸው አፍሪካ ከቻይና የምታገኘው ብድር ወደማይወጡት አዘቅት እንዳይከታት ከማስጠንቀቅ ወደ ኃላ አላሉም።

ሺ ዢፒንግ ትርፋማ የሆኑ ዘርፎችን ለይቶ፤ በቻይናና አፍሪካ መሀከል ያለውን ትብብር ዳግም መቃኘት እንደሚያስፈልግ በጉባኤው ላይ ተናግረዋል። "የቻይናና የአፍሪካ ጥምረት በዋነኛ የልማት ስራዎች ላይ ያነጣጠረ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

የቻይና ኢንቨስትመንት ለአፍሪካ ጠቀሜታ በሚሰጡ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

አፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን የቻይና ኢንቨስትመንት ያወደሱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ "አንዳንዶች አፍሪካ በአዲስ አይነት ቅኝ ግዛት ስር ወድቃለች ከሚሉት ጋር አልስማማም" ብለዋል።

በፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ ገለጻ አፍሪካ ውስጥ ያላቸው ኢንቨስትመንት "ከፖለቲካ ጋር የተነካካ አይደለም"።

የተመደበው 60 ቢሊየን ዶላር ለመሰረተ ልማትና ለወጣቶች ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት ይውላል።

ለአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት፤ ቻይና ወታደራዊ ስልጠና መስጠቷን እንደምትቀጥል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አክለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2000 እስከ 2016፤ ቻይና ለአፍሪካ 125 ቢልየን ዶላር ማበደሯን ጥናቶች ያሳያሉ።

ገንዘቡ በቀዳሚነት በመንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የወደብ ዝርጋታ ላይ ውሏል።

ከኬንያ መዲና ናይሮቢ እስከ ሞምባሳ የተዘረጋውና 3.2 ቢሊየን ዶላር የወጣበት ባቡር ሀዲድ በብድሩ ከተሰሩ መካከል ይጠቀሳል።

ወደብ አልባዎቹ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ብሩንዲን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ያስተሳስራል ተብሎ ይጠበቃል።