የማክሰኞ ምሽት አጫጭር ዜናዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የውጭ ኩባንያዎች በሎጅስቲክስ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተፈቀደ። ይህ ኩባንያዎቹ እቃዎችን በማሸግ፣ በማስተላለፍና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት እንዲሰማሩ ያስችላል።
- ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን 12 ሰዎች ሲሞቱ አራት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
- አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ታስረው እንዲሰቃዩ ተደርጓል አለ። አብዛኞቹ እስረኞች ተቃዋሚዎችና ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ እንደሆኑም አምነስቲ አስታውቋል።
- የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ጃን ፔሪ ቤምባ በመጪው ምርጫ እንዳይወዳደሩ ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ቤምባን ያገዳቸው ከዚህ ቀደም በአለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ተከሰው ስለነበር ነው።
- የጣልያን መከላከያ ሚኒስትር ኤልዛቤታ ትሬንታ ለዛሬው የሊቢያ ቀውስ ፈረንሳይ ከፊል ተጠያቂነት አለባት አሉ።ፈረንሳይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሊቢያ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት ስታደርግ የራሷን ፍላጎት አስቀድማ ነውም ብለዋል፣ ሚኒስትሯ።
- ግብፅ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ለአንድ የስፔንና ጣልያን የሽርክና ኩባንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንድትከፍል ተፈረደባት። ግብፅ በአረብ አብዮት ጊዜ በገባችው ውል መሠረት ለኩባንያው ጋዝ ባለማቅረቧ ነው ውሳኔው የተላለፈባት።
- ብራዚል በቃጠሎ የወደመባትን ጥንታዊ ሙዚየም መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ እርዳታ ጠየቀች። ጥሪውን ተከትሎ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ለብራዚል እርዳታ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።
- የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ልጆችን በማሰረቅ የተከሰሱት ስፔናዊው ዶክተር ዛሬ በማድሪድ ፍርድ ቤት ቀረቡ። የ85 ዓመቱ አዛውንት ከአስርት አመታት በፊት በስፔን የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ልጆች በወቅቱ የአገሪቱ መሪ ጀነራል ፍራንሲስኮ ፍራንኮ ደጋፊዎች በማደጎ እንዲያድጉ ያደርጉ ነበር ተብሏል።