የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ለምን ታሰሩ?

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሥራ ማቆም አድማ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ የጠየቅነው የጥቅማጥም ጥያቄዎች መልስ አላገኙም በማለት ነበር የሥራ ማቆም አድማ የመቱት። ትናንት ማምሻውን ደግሞ 9 የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ይሄን ተከትሎ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋል የህግ አግባብነትን በተመለከተ ጥያቄዎችን አጭሯል።ለመሆኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሥራ ማቆም አድማ የማድረግ መብት የላቸውምን?

የመንግስት ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መምታት እንደሚችሉ በህገ መንግስቱም ሆነ በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ 377/96 ላይ መደንገጉን የሚጠቅሱት የህግ ባለሙያው አሃዲ ደቀቦ በተወሰኑ የሥራ መስኮች ውስጥ የመንግሥት ሰራተኞች ግን በልዩ ሁኔታ የሥራ ማቆም አድማ ውስጥ መሳተፍ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።

ከእነዚህም መካከል የአየር መንገድ እና የሆስፒታል ሰራተኞችን ለአብነት ያነሳሉ።

«ይሁንና ይሄ አዋጅ (የአየር ትራፊኮችን) በመሰሉ የሲቪል አቪዬሽን ተቀጣሪዎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን አይደለም። መ/ቤቱ የተቋቋመበት የሲቪል አቪየሽን አዋጅ 616/2001 አለ። ሰራተኞችም የሚተዳደሩት በዚህ አዋጅ ነው። በዚህም ሆነ ቀጥሎ በወጡ አዋጆች ላይ እኚህ ሰራተኞች (የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች) የስራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደማይችሉ የሚደነግገው ነገር የለም።» ሲሉም ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በበኩላቸው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ለእስር የተዳረጉት የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ሳይሆን ''የኢትዮጵያ የአየር ደህንነት አደጋ ላይ ነው በማለታቸው ነው'' ይላሉ።

«በብዛት የኢትዮጵያ የአየር ክልል አደገኛ ነው በማለት በመቀስቀስ የአቪየሽኑን ስም ያበላሹ ናቸው (የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች)። የሌለን ነገር ፈጥሮ መፃፍ ትክክል አይደለም።የኢትዮጵያን አየር ክልል ለሚጠቀሙ በቀጥታ በመፃፍ እንዲሁም የጎረቤት ሀገራት የባለሙያዎች ማህበራትን በመጠቀም ሀገሪቱን ችግር ላይ ለመጣል የታገሉ ናቸው» ሲሉ ይከሳሉ።

በሌላ በኩል፤ ማንኛውም ዜጋ የመናገር መብቱ በህገ-መንግስቱ እና በሌሎች ህጎች ላይ ስለመከበሩ የሚያስረዱት የህግ ባለሙያው አሃዲ ደቀቦ ይህ መብትም በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች እንደሚገደብ ያስገነዝባሉ።

የትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹን ድርጊት አቃቢ ህግ ከወንጀል ቆጥሮ ክስ የከፈተው የወንጀል ህጉን አንቀፅ 505 መሰረት አድርጎ ሳይሆን እንደማይቀርም ያትታሉ።

«በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንቀፅ 505 ላይ የየብስ ፣የውሃ እና አየር የመገጓዣ መንገዶችን መደበኛ አሰራር በማናቸውም መንገድ ማወክ ወንጀል መሆኑን ያስቀምጣል። በማናቸውም መንገድ የሚለው የተግባር (የድርጊት) አሊያም የንግግር ሁከትን ያጠቃልላል።» ሲሉ ይጠቅሳሉ።

የህግ ባለሙያው ፣ ዐቃቢ ህግ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ድርጊት መደበኛውን የአየር ትራንስፖርት ማስተጓገሉን በማስረጃ በማስደገፍ የማስረዳት እና ፍ/ቤቱን የማሳመን ግዴታ እንዳለበት አፅንኦት ይሰጣሉ። ዐቃቢ ህግ ይሄንን ካስረዳ ጉዳዩ እስከ 5 ዓመት ድረስ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ያሰምሩበታል።

ሆኖም ተከሳሾቹ ስሜት እና እምነታቸውን የገለፁበት መንገድ መደበኛ ስራን ያላስተጎገለ ፤ተፈላጊው የምክንያት እና ውጤት ግኑኝነት እንደሌለው ከታመነ የተቆጣጣሪዎቹ ድርጊት የንግግር መብትን ከመጠቀም የዘለለ ለቅጣት የሚያበቃ ወንጀል ተደርጎ እንደማይወሰድ ባለሙያው ያብራራሉ።