የህንድ ፖሊስ የወርቅ ምሳ እቃ የሰረቁ ዘራፊዎችን እየፈለገ ነው

የተሰረቀው የወርቅ ምሳ እቃ
የምስሉ መግለጫ,

የተሰረቀው የወርቅ ምሳ እቃ

ከወርቅ የተሰራ የህንድ ንጉሳውያን ምሳ እቃ መዘረፍን ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው። ምሳ እቃው በወርቅ ተሰርቶ በእንቁ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ ሲሆን፤ ባለቤቶቹ የቀድሞ ንጉሳውያን ቤተሰቦች ናቸው።

ሀይደርባድ የተባለችው ከተማ ፖሊሶች ከምሳ እቃው በተጨማሪ ከወርቅ የተሰራ የሻይ ሲኒ እና ማንኪያም እያፈላለጉ ይገኛሉ።

የተሰረቁት እቃዎች ወደ 3 ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝኑና ዋጋቸው 7 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ናቸው።

የንጉሳውያን ቤተሰብ ንብረቶቹ እንደተሰረቁ የታወቀው ሰኞ እለት ነበር።

ፖሊሶች እንደሚሉት እሁድ ምሽት ቁሳ ቁሶቹ ከሚገኙበት ሙዚየም ነበር የተወሰዱት።

ሌቦቹ የሙዚየሙ ስውር ካሜራዎችን በማበላሸት ስርቆቱን እንደፈጸሙ ፖሊሶች ተናግረዋል።

የተዘረፉት ቁሳ ቁሶች ባለቤት የህንዷ ሀይደርባድ ከተማ የመጨረሻው ንጉስ ነበር።

ሚር ኦስማን አሊ ካሀን የሚባለው ንጉስ በአንድ ወቅት በአለም ላይ በሀብት መጠኑ ተወዳዳሪ አልነበረውም።

ከአስር ዓመት በፊት የዚሁ ንጉሳዊ ቤተሰብ ንብረት የሆነ ጎራዴ ተሰርቆ ነበር።

በወቅቱ በስርቆቱ እጃቸው እንዳለ የተጠረጠሩት ሁለት ግለሰቦች ነበሩ።

ናዚም በመባል የሚጠራው ሙዚየም ለህዝብ ክፍት የሆነው እንደ አውሮፓውያኑ በ2000 ነበር።

ለሚር ኦስማን አሊ ካሀን የተበረከቱ ውድ ስጦታዎች በሙዚየሙ ይገኛሉ።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1967 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ንጉሱ፤ "ጃኮብስ ዳይመንድ" መበባል የሚጠራውና የእንቁላል መጠን ያለው እንቁ ባለቤት ነበር።