አውስትራሊያዊው አዛውንት ከመሞታቸው በፊት አይስ ክሬም ለመብላት ጠይቁ

የ72 ዓመቱ አዛውንት አይስ ክሬም በልተዋል

የፎቶው ባለመብት, QUEENSLAND AMBULANCE SERVICE

የምስሉ መግለጫ,

የ72 ዓመቱ አዛውንት ከመሞታቸው በፊት አይስ ክሬም በልተዋል

"ምን መብላት ይፈልጋሉ?" በጠና ለታመሙ የ 72 ዓመት አውስትራሊያዊ አዛውንት የቀረበ ጥያቄ ነበር። አዛውንቱ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለዩበት ቀን ደርሶ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ህክምና መስጫ እየተሰወዱ ሳለ ነበር መብላት የሚፈልጉትን የተጠየቁት።

ወደ ህክምና መስጫ እየወሰዳቸው በነበረው አምቡላንስ ውስጥ ሳሉም "አይስክሬም ብበላ እወዳለሁ" ብለው ሮን ማክተርኒ የተባሉት አዛውንት መልስ ሰጡ። የህክምና ባለሙያዎቹ አላንገራገሩም። የአዛውንቱ ምርጫ የሆነውን የካራሜል ጣዕም ያለው አይስ ክሬም ሰጥተዋቸዋል።

ለ 17 ዓመታት በጣፊያ ካንሰር ይሰቃዩ የነበሩት አዛውንት ህይወታቸው ያለፈው ባለፈው ቅዳሜ ነበር። ልጃቸው በፌስቡክ ገጿ "አባቴ ለመጨረሻ ጊዜ ያለ ሰው እርዳታ መብላት የቻለው አይስ ክሬም ነበር፤ በጣም ጣፍጦት ነበር" ብላ ጽፋለች።

አይስ ክሬሙን ለአዛውንቱ የሰጧቸው የህክምና ባለሙያዎች ለተግባራቸው እየተመሰገኑ ነው። በተለይም የሮን ማክተርኒ ቤተሰቦች የህክምና ባለሙያዎቹ አዛውንቱ ለቀናት ምግብ በአፋቸው እንዳልዞረ ተገንዝበው፤ ያማራቸውን አይስ ክሬም በመስጠታቸው ተደስተዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ተግባር ፈጽመዋል። ለመሞት ቀናት የቀሯት ሴት ወደ ባህር ዳርቻ የመሄድ የመጨረሻ ፍላጎቷን አሟልተውላት ነበር።

የህክምና እርዳታ በተለያየ መንገድ መሰጠቱ እሙን ነው። እነዚህ ሀኪሞች ደግሞ ሊሞቱ ቀን የሚቆጥሩ ህመምተኞችን ህልም እውን በማድረግ የድረሻቸውን እየተወጡ ነው።