ናይጀሪያ፦ ኤምቲኤን ኩባንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ግብር ተጣለበት

ኤምቲኤን በአፍሪካ ትልቁ የቴሌኮም ኩባንያ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ናይጀሪያ ኤምቲኤን ተብሎ የሚጠራው የቴሌኮም ኩባንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ግብር እንዲከፍል አዘዘች።

ኩባንያው በበኩሉ የግብሩ መጠን ትክክለኛ እንዳልሆነና የባለፈው አስር አመታትንም እንዳስገባ ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም 700 ሚሊዮን ዶላር እንደከፈሉም አስታውቀዋል።

ይህ የግብር ጥያቄ በኤምቲኤንና የኩባንያው ትልቋ ገበያ በሆነችው በናይጀሪያ ተከታታይ እሰጣገባዎች አዲሱ ነው።

ኩባንያው ከሁለት አመታት በፊት ያልተመዘገቡ ሲም ካርዶችን ከመስመር ውጭ ባለማድረጉ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ሊከፍል ተስማምቶ ነበር።

ባለፈው ሳምንት የናይጀሪያው ማዕከላዊ ባንክ ኩባንያው ከሀገሪቱ በህገወጥ መንገድ ያስወጣውን ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

በአህጉሪቷ ውስጥ ካሉ ኩባንያዎች ግዙፉ ኤምቲኤን በበኩሉ ይህ ግብር የናይጀሪያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያደረገውን ምርመራ ተከትሎ ሲሆን፤ ይህም የተለያዩ ቁሶችን ከውጭ ሀገር በማስገባትና ዕቃዎቹንም ለማስመጣት በአስር አመት ውስጥ የተከፈለ ክፍያ ነው ብለዋል።

ጨምረውም የናይጀሪያ መንግሥት የሚጠይቀውን ግብር ሙሉ በሙሉ ከፍለናል ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካዋ የንግድ መዲና ጆሀንስበርግ የሚገኘው ኤምቲኤን በከፍተኛ ሁኔታ የገበያ ሁኔታው እንዳሽቆለቆለ ተነግሯል።