አምሳለ ዋካንዳ በጢስ አባይ ይገነባ ይሆን?

በብላክ ፓንተር ፊልም ላይ በምናብ የተሳለው ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Hubcity Live Document

የምስሉ መግለጫ,

በብላክ ፓንተር ፊልም ላይ በምናብ የተሳለው ከተማ ገፅታ

በብላክ ፓንተር ፊልም ላይ በምናብ የተሳለው ዋካንዳ ከተማ በኢትዮጵያ በዕውን ሊሰራ መሆኑ ከተገለፀ አንስቶ የበርካቶች መነጋጋሪያ ሆኗል።

ከተማው በአንድ በኩል የአፍሪካውያን የባህልና የታሪክ ማንነት መገለጫዎች የሚሰባበሰቡበት ፣ በሌላ በኩል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምርምር የሚካሔድበት፣ ሮቦቶች የሚርመሰመሱበት፣ ሮኬት የሚመጥቅበት ፣ በሌላኛው ገፅ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት እና የሚከናወንበት የኢንዱስትሪ ክፍለ ከተማ፤ የሚገማሸረውን የአባይ ፏፏቴንና ሸንተረሮቹን ጠዋት ማታ አሻግሮ ለማየት በሚያመች መልኩ ይገነባል ተብሏል።

ይሁን እንጂ ዕቅዱን ቅዠት ነው፤የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላጋናዘበ ነው ሲሉ ያጣጣሉትም አልታጡም።

ፕሮጀክቱ ሀብ ሲቲ ላይቭ በሚባል ፕሮጀክት ስም በፊልሙ ላይ የሚታየውን የምናብ ከተማ በእውነት ለመገንባት ታቅዷል።

"ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች መኖሪያ፣ የቀደመ ስልጣኔ ምንጭና መገኛ ቦታ ነች፤ ስለዚህ ምንጩ ላይ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች የሚጋሩትንና በቴክኖሎጂም በባህልም የበለፀገ ከተማ እንገንባ የሚል ሃሳብ ያለው ነው" ይላሉ በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታሁን መኮንን።

ሀብ ሲቲ ላይቭ የቴክኖሎጂ ከተማውን ዋካንዳን ካሊፎርኒያ ውስጥ ለመገንባት የቀደመ ሃሳብ ቢኖረውም፤ እውነተኛ ዋካንዳ ግን አፍሪካ ለዚያውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው መሆን ያለበት በሚል በደቡብ ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በባህርዳር የሚገኙ ቦታዎችን ሲያስስ መቆየቱን የሚናገሩት ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲዔታ የሆኑት ዶክተር ሹመቴ ግዛው ናቸው።

በመጨረሻም በአማራ ክልል የሚገኘው ጢስ አባይ በፊልሙ በምናብ ከተሳለው የቴክኖሎጂ ከተማው (ዋካንዳ) ጋር ተመሳስሎ በማግኘታቸው የክልሉን መንግስት ጋር ንግግር እንደተጀመረ ይገልፃሉ።

ከክልሉ መንግስት ይሁንታ ከተገኘ በኋላ ሃሳቡ የቴክኖሎጂ ከተማን መገንባት በመሆኑ ድርጅቱ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር መወያየት እንደጀመረ ዶክተር ሹመቴ ይናገራሉ።

ጢስ ዓባይ ላይ ይገነባል የተባለው የቴክኖሎጂ ከተማ ገፅታ

የፎቶው ባለመብት, HubCity Live Facebook

የምስሉ መግለጫ,

ጢስ ዓባይ ላይ ይገነባል የተባለው የቴክኖሎጂ ከተማ ገፅታ

ፕሮጀክቱ ቴክኖሎጂን ከማሳደግ፣ቱሪዝምን ከማስፋፋት፣ ኢንቨስትመንትን ከማበረታታቱ የሚኖረውን አስተዋጽኦ በማለም ሃሳቡን ወደዱት፤ የመጀመሪያው የምክክር መድረክም በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ተካሄደ።

በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ ሁለተኛው ውይይት ይደረጋልም ብለዋል።

ተፈጥሮውን ከመጠበቅ ጋር የሚጋጭ ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ኮሚሽነር ጌታሁን መኮንን "ሌሎች የሐይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ በመዘየድ የጢስ አባይ ፏፏቴ ወደ ቀድሞው ግርማው መመለሱ የፕሮጀክቱ አካል ነው" ሲሉ ይገልፃሉ።

የፕሮጀክቱ ጥናት

በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታሁን ሁብ ሲቲ ላይቭ ይዞ የመጣው ሃሳብ ዱብ እዳ ሳይሆን ላለፉት 7 ዓመታት ጥናት እንደተደረገበት ያስረዳሉ።

"የጥናቱ ውጤትም በተለያየ ጊዜ ይገለጽልን ነበር" ብለዋል።

ብላክ ፓንተር ፊልም ለዕይታ የበቃው በአውሮፓውያኑ ጥር 2018 ነው፡፡ በእርሳቸው ንግግር ፊልሙ የጥናቱ የልጅ ልጅ ቢሆን ነው።

ሁለቱን የሚቃረኑ ሃሳቦች አድምጠን በጥናቱ ላይ የተሳተፉት እነማን ናቸው ስንል የጠየቅናቸው ኮሚሽነሩ፤

"በጥናቱ ባለቤትነት ደረጃ ተሳትፈናል ማለት የሚቻል አይመስለኝም" ሲሉ መልሰዋል፤ ይሁን እንጂ ለከተማው ግንባታ ወደተመረጠው ቦታ በመሄድ የተመለከቱ ባለሙያዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

ይህንኑ ጥያቄ የሰነዘርንላቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲዔታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው

"ባለኝ መረጃ መሰረት ፊልሙን ለመስራት የተሰራ ጥናት ካልሆነ በስተቀር፤ ከተማውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የታሰበው ፊልሙ ከወጣ በኋላ ነው" ይላሉ።

የፕሮጀክቱ ሃሳብ ወደ መስሪያ ቤታቸው ከመጣ በጣም አጭር ጊዜ እንደሆነ ባይክዱም፤ "ፊልሙን ለመስራት ሲታሰብ ብዙ የተሰራ ጥናት ሳይኖር አይቀርም" ሲሉም የምናልባት ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

በሃሳብ ደረጃ ያለው ሌላኛው ገፅታ

የፎቶው ባለመብት, HubCity Live Facebook

የምስሉ መግለጫ,

በሃሳብ ደረጃ ያለው ሌላኛው ገፅታ

በ20 ቢሊየን ዶላር የሚገነባን ትልቅ የፕሮጀክት ሃሳብ ጋር በዚህ አጭር ጊዜ መዋሃድ ያስችላል ወይ ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ሹመቴ፤

"አንድን ነገር ለመረዳት አንድ ቀን፣ አንድ ወር አሊያም አስር ዓመት ሊወስድ ይችላል፤ነገር ግን አስር ዓመት የሚፈጀውን በአንድ ቀን ተገንዝቦ መጨረስ ከተቻለ በቂ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።

ሊያሳስበን የሚገባው ከጊዜው ይልቅ ጠቀሜታው ነው ይላሉ።

ሀብ ሲቲ ላይቭ ማነው?

ሀብ ሲቲ ላይቭ ይህ ፕሮጀክት ሲነሳ ተደጋግሞ የሚነሳ ስም ነው፤ በአሜሪካ አገር የሚገኝ ድርጅትና የፕሮጀክቱ ሃሳብ አፍላቂም ተደርጎ ይነገራል። ሀብ ሲቲ ላይቭ ማነው?

በእኛ በኩል ስለ ድርጅቱ ለማወቅ ጥረት ብናደርግም ጥቂት ሰዎች ከወደዱት የፌስቡክ ገፅና በቅርቡ አገልግሎት እንደሚሰጥ ከሚገልፅ ድረ -ገፅ (www.hubcitylive.com) በስተቀር በቂና የተደራጀ መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

ይህንኑ አስመልክተን የጠየቅናቸው ሚኒስትር ዲዔታው የቴክኖሎጂ ከተማ የመገንባቱን ሃሳብ በምክክር መድረኩ ወቅት ያቀረበው ሚካኤል ካሚል የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ እንደሆነና በመስሪያ ቤቱም በተደጋጋሚ ሲመላለስ ያዩት እርሱን እንደሆነ ገልጸውልናል።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ አሊያም ከመስሪያ ቤቱ ጋር የቀደመ የስራ ግንኙነት ስለመኖር አለመኖሩም ዕውቅናው እንደሌላቸው ተናግረዋል።

"ያገኙትን አፍሰው ቢበሉት፣

ያስቸግር የለም ወይ ሲውጡት" እንዳለችው ድምጻዊቷ

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እንዴት ስምምነት ላይ መድረስ ተቻለ ያልናቸው ሚንስትር ዲዔታው፤

የአንድን ፕሮጀክት ተግባራዊነት ደረጃ የማወቂያ ጥናት (Feasibility study) ሃሳባዊ፣ ቅድመ ትግበራና ትግበራ በሚባሉ ሶስት ደረጃዎች ማለፍ እንደሚገባው ያብራራሉ።

በመሆኑም "ፕሮጀክቱ በሃሳባዊ ደረጃ ያለ በመሆኑ፤ ግንዛቤ የመፍጠርና ፕሮጀክቱን የማስተዋወቅ ስራ ነው የሚሰራው፤ እኛም እሱ ላይ ነን" ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት ጥቅምና ጉዳቱን፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ ተግዳሮቶችና ሌሎች ጥናቶች ይደረጋል፤ የጥናቱ ውጤት ታይቶ ፕሮጀክቱ ሊቀር ይችላል፤ በከፊል ሊስተካከል ይችላል፤ አሊያም እንዳለ ሊቀጥል ይችላል።

ይህ ፕሮጀክትም ከሶስቱ የአንዱ እጣፈንታ ሊገጥመው ይችላል ይላሉ።

ቴክኖ ቱሪዝምን፣ ፈጠራንና ኢንዱስትሪን ያስፋፋል ብለው በማመናቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱን በሃሳብ ደረጃ እንደተቀበለው ደጋግመው ያስረዳሉ።

የገንዘብ ምንጩ

20 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚፈጅ የተገመተለት ይህ ፕሮጀክት ምንጩ ምንድን ነው?

አቅም ያላቸውና በዓለም ላይ የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ተባብረው ይገነቡታል፤ ዋናኛው የገንዘብ ምንጭም በተለያየ ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቁር አሜሪካውያን ባለሃብቶች እንደሚሆኑም ይታመናል።

ሌላኛው የከተማው ከፊል ገፅታ

የፎቶው ባለመብት, Hubcity Live Facebook

የምስሉ መግለጫ,

ሌላኛው የከተማው ከፊል ገፅታ

ሃሳቡን የሚደግፉ ሁሉ ከተማዋን እንዲገነቡ ይደረጋል፤ በተለይ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሃብቶች ድርሻ ከፍ እንዲል ጥረት እንደሚደረግ ኮሚሽነር አቶ ጌታሁን መኮንን ይገልፃሉ።

"ድርጅቱ ሃሳቡን ይዞ የመጣው፤ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደሚቻል አምኖ ነው" የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ሹመቴ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ከድርጅቱ ጋር በነበራቸው ውይይትም እውነተኛውን የቴክኖሎጂ ከተማ ለማየት ፍላጎት ያላቸው በርካታ ግለሰቦች እንዳሉ ተገልጾላቸዋል።

በመሆኑም የሚጠቅም ሆኖ እስከተገኘ ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡበት ምክንያት እንደሌለና እንደ መስሪያ ቤት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ያረጋግጣሉ።

"ይህ የሚሆነው ግን ጥናቱ ተጠናቆ መተማመኛ ሲገኝ ነው" ይላሉ።

ከፈረሱ ጋሪው?

የተሟላ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ የተስተካካለ መንገድ፣ በክህሎትና በዕውቀት የዳበረ የሰው ኃይል ባልተበራከተበትና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ልማቶች ባልተሰሩበት ስለ ፕሮጀክቱ ማሰብ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ የሚሉት ጥቂት አይደሉም።

የኢትዯጵያ መንግስት 20 ቢሊየን ዶላር አወጣለሁ ብሎ ቢነሳ፤ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ያስብላል የሚሉት ዶ/ር ሹመቴ

"ጥቅም ያለውና በጀቱ ከሌላ ቦታ ሊገኝ የሚችል ፕሮጀክት ሲመጣ፤ እኛ አንፈልግም እዚህ ደረጃ ላይ አልደረስንም ማለት ግን አንችልም" ብለዋል።

አቶ ጌታሁን መኮንን በበኩላቸው "ስራው በአገር ውስጥ ያለውን ዝግጁነት የሚጠይቅ አይደለም፤ ይህም በአገር ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች የሚያጓድል አይደለም፤ ለከተማው ያስፈልጋል የሚባሉት መሰረተ ልማቶች አብረው የሚከናወኑ በመሆናቸው የመንግስትን በጀት የሚነካ አይደለም ይላሉ።

በአገራችን ተጀምረው መቋጫው የተጣፋባቸው ፕሮጀክቶች ለዚህኛውስ የስጋት ማሳያ አይሆኑም ወይ ያልናቸው ዶ/ር ሹመቴ

ተጀምረው የቀሩ እንዳሉ በማመን አሁንም መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል፤ ነገር ግን ለተግባራዊነቱ ተባብሮና አስተሳስሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

"ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ አዲስ ሃሳብ ያላቸውና ስጋት የገባቸው ወደኛ ይዘው ቢያቀርቧቸው እንደ ግብዓት እንጠቀምበታለን" ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በበላይነት የሚቆጣጠረው ማነው?

ዶ/ር ሹመቴ "እንደነዚህ ዓይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚመራው ማነው? የሚለውን ለመወሰን ጊዜው አሁን አይደለም" ይላሉ።

ገዳዩ ከቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ጋር ግንኙነት የተጀመረ ቢሆንም አሁን ባለበት ደረጃ በስም፣ በሀብት፣ በሃላፊነት እገሌ ነው ብሎ መጥቀስ እንደማይቻል ይናገራሉ።

የሚገነባው ከተማ ሰፊ በመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነት ይኖራቸዋል፤ በየ ዘርፋቸው ተሳትፎ ያደርጉበታል ያሉን ደግሞ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌታሁን መኮንን ናቸው።

ፕሮጀክቱ በአስር ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎም እንደተገመተ ተገልጿል።