የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች አሥመራ ላይ ይመክራሉ

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቻይና መልስ ወደ ኤርትራ ለሁለተኛ ጊዜ አቅንተው አሰብ ላይ በሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በተመሳሳይም በዛሬው እለት ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ የጭነት መርከብ በምፅዋ ወደብ ላይ ምልህቋን በመጣል ወደ ቻይና የሚላክ ጭነት እንደምታጓጉዝ ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በቅርቡ ለኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል የተባለውን የአሰብ ወደብን ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር የሚያገናኝ የየብስ መንገድ መንገድ ያለበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ወራት ውስጥ በኤርትራ ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከአሰብ ወደ አሥመራ ከማቅናታቸው በፊት የምፅዋ ወደብንም ይጎበኛሉ ተብሏል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኤርትራ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ የፈጠሩት ግንኙነትና ያስቀመጡት ዕቅድ ያለበትን ሁኔታን በተመለከተ እንደሚወያዩ ተነግሯል።

በተያያዘ ዜና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ወደ ኤርትራ እንደሚያቀኑ የሃገሪቱ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሳውቋል።

መስሪያ ቤቱ እንዳመለከተው ፕሬዝዳንቱ ሃሙስና አርብ አሥመራ ውስጥ ይካሄዳል በተበላ የኤርትራ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ትብብር ጉዳይ ላይ በሚያተኩር ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ ብሏል።

ይህም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኤርትራ ጉዞ ይህንን የሦስት ሃገራት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ያለመ እንደሆነም ይታመናል።