አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው?

የተበከለ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Ed Wray

በትግራይ ክልል በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ወረርሽኝ የአስር ሰዎች ህይወት አልፏል። ወረርሽኙ በተለይ በማዕከላዊ ዞን ሃፈሮም ወረዳ ብዙ ሰዎችን አጥቅቷል።

በትግራይ ክልል የበሽታው ምልክቶች ከሰኔ 11 ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መታየት እንደጀመሩና ተጠቂዎቹ ወደ ህክምና ቦታዎች በመሄድ ህክምና እንዳገኙ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተክላይ ወልደማርያም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከነሃሴ አጋማሽ ጀምሮ በሳምንት እስከ ስድስት የሚደርሱ ህመምተኞች በተለያዩ የህክምና መስጫ ቦታዎች ክትትል ሲደረግላቸው እንደነበረና ከዚያ በኋላ ግን ቁጥሩ እየጨመረ እንደመጣ ይናገራሉ።

በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ዞን ሃፈሮም ወረዳ ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ የሚሆኑ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ለጸበል አገልግሎት የሚጠቀሙት ቦታ ላይ በተነሳ ወረርሽኝ 400 የሚሆኑ ሰዎች ታመዋል።

በሁኔታው የተደናገጡ ቦታው ላይ የነበሩ ሌሎች ምዕመናን አካባቢውን ለቀው ወደ መጡበት ሲመለሱ፤ የበሽታው ምልክቶች በሌሎች አካባቢዎችም መታየት እንደጀመረ አቶ ተክላይ ያስረዳሉ።

በቅርቡም በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ውስጥም አንዳንድ ምልክቶች መታየት የጀመሩ ሲሆን፤ አጠቃላይ በክልሉ 1266 የሚሆኑ ነዋሪዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸውን ሃላፊው ተናግረዋል። አስር ሰዎችም ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ማለፉን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አረጋግጠውልናል።

ከሃፈሮም ወረዳና መቀለ ከተማ በተጨማሪ በምዕራባዊ የክልሉ ዞኖች በተለይም በእርሻና ባህላዊ የማዕድን ለቀማ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ነዋሪዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ምክትል የቢሮ ሃላፊው ነግረውናል።።

አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው?

''አተት ወይንም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በራሱ አንድ በሽታ አይደለም፤ የበሽታ ምልክት ነው። እንደ ቫይረስ፤ ባክቴሪያና የምግብ መበከል ባሉ የተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱ በሽታዎች ምልክት ግን ሊሆን ይችላል" ይላሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን።

ምልክቶቹን ብቻ በማየት ግን ኮሌራ ነው ብሎ መደምደም እንደሚከብድ ፤ ከታካሚው ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ተገቢው ምርመራ ከተደረገ በኋላ ውጤቱን በማየት ብቻ ነው ኮሌራ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚቻል ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

''በአብዛኛው ህብረተሰብ ውስጥ ያለው የተሳሳተ አመለካከት አተት ሁሉ ኮሌራ እንደሆነ ነው። አተት ሁሉ ግን ኮሌራ ማለት አይደለም፤ ኮሌራ አንድ ሰው ላይ ከተገኘ ምልክቱ የሚሆነው አተት ነው።'' በማለት አክለዋል ዶክተር አሚር።

''አተት በራሱ በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፤ ኮሌራ ደግሞ ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሊሆን እንደሚችል ሚኒስተሩ ያስረዳሉ። ኮሌራ ካለ ሁሌም ቢሆን አተት ይኖራል፤ አተት ሲከሰት ግን በብቸኝነት ኮሌራ ነው ያስከተለው ማለት አንችልም። ምክንያቱም አተትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ብዙ የጤና እክሎች ስላሉ።''

የግል እና የአካባቢን ንጽህና የመጠበቅ ዝቅተኛ ልምድ ባለባቸው አካባቢዎችና ያልበሰሉ ምግቦች ጥቅም ላይ በሚውሉባቸው ቤቶች ውስጥ ሁሌም ቢሆን ኮሌራን ጨምሮ አተት ዋነኛ ምልክታቸው የሆኑ የተለያዩ በሽታዎች እንደሚከሰቱ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

መቀለ የክልሉ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ብዙ የጥንቃቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት ሲጠበቅባቸው ፤ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ወረርሽኙ በተደጋጋሚ ተከስቷል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ?ስንል ለአቶ ተክላይ ጥያቄ አቀረብንላቸው።

''የመቀሌ ከተማ ከታሰበው ፍጥነት በላይ እያደገችና እሰፋች ነው። ከገጠር ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው የሰው ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፤ በዙሪያዋ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችም ተገቢው የከተማ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው ናቸው።''ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የከተማው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር ሲወዳደር አጥጋቢ የሚባል አይደለም። ምንም እንኳን አገልግሎቱን ለማሻሻል ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ንጹህ የመጠጥ ውሃ በሚገባው መጠንና ጥራት እያገኘ አይደለም።

ምክትል የቢሮ ሃላፊው አክለውም በተለይ ደግሞ በከታማዋ ያለው በቂ ያልሆነ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ ከገጠር ወደ ከተማ የሚገቡት የማህበረሰብ ክፍሎች የከተማ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ የመገንባትና የመጠቀም ልምድ አለመኖር ወረርሽኙ ቶሎ ቶሎ እንዲነሳንና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዳሉ።

ወረርሽኙ ተነሳበት የተባለውና በሃፈሮም ወረዳ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የሚፀበሉባቸው ቦታዎችን በተመለከተ፤ የጸበል ቦታዎቹ በብዛት የተቋቋሙት ወራጅ ወንዞችን ተከትለው ስለሆነ፤ በተለይ በክረምት ወራት ለብክለት የተጋለጡ እንደሚሆኑ ያመለክታሉ።

በመጨረሻም ጉዳዩ ከአካባቢው ማህበረሰብ ሃይማኖት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ በዋነኛነት ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በሃይማኖት ተከታዮቹ ጥንቃቄና የመከላከል ስራ እንደሆነ አቶ ተክላይ ጠቆም አድርገዋል።