የረቡዕ ምሽት አጫጭር ዜናዎች

የፎቶው ባለመብት, CBS
• የኬንያ ፖሊስ ዛሬ ናይሮቢ የሚገኘው የቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ቢሮን ፈተሸ። ፖሊስ ቻይናዊያንን ጨምሮ 13 የቢሮውን የውጭ አገር ዜጋ ሰራተኞችን ወስዶ የስራ ፈቃድ እንዳላቸው ካረጋገጠ በኋላ ለቋቸዋል።
• የናይጄሪያ ብሄራዊ እግርኳስ ቡድን አሰልጣኝ ለአንድ ዓመት ከስፖርት ታገዱ። ሳሊሱ የሱፍ የታገዱት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2018ቱ የቻን ውድድር ተጫዋች ምርጫ ጋር በተያያዘ ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
• በኤምሬትስ አየር መንገድ ከዱባይ ወደ ኒውዮርክ የበረሩ መንገደኞች በመታመማቸው አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ ሰው ሁሉ ከአውሮፕላን እንዳይወርድ ተደረገ። አየር መንገዱ የታመሙት አስር መንገደኞች ብቻ ናቸው ቢልም፤ የኒውዮርኩ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አውሮፕላን ማረፊያ ግን የመንገደኞቹ ህመም ምን እንደሆነ ሳይታወቅ መንገደኞቹ ከማንም እንዳይቀላቀሉ አድርጓል።
• ከአራት መቶ የሚበልጡ የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞችን በኒጀር በርሃ እንዳገኘ የአለም ስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም አስታወቀ። ስደተኞቹ ማሊ፣ ጊኒና ሴኔጋልን ጨምሮ ከ13 አፍሪካ አገራት በእገር ተጉዘው ከበርሃው የደረሱ እንደሆኑም ድርጅቱ አስታውቋል።
• የአለም ጤና ድርጅት አካላዊ እንቅስቃሴ ባለማድረግ ከአራት ሰዎች የአንዱ ጤና አደጋ ላይ እየወደቀ ነው አለ። የድርጅቱ ሪፖርት እንዳለው ከአለም ህዝብ አንድ አራተኛው በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አያደርግም። ከአለም ደግሞ ጥሩ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚደረግባት አገር ኡጋንዳ መሆኗ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
• በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በአንድ ህንፃ ላይ የተነሳን እሳት ለማጥፋት ሲሰሩ ከነበሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች ሶስት ሞቱ። አንደኛው የነፍስ አድን ሰራተኛ ከሄሊኮፕተር በመውረድ ላይ ሳለ ወድቆ በቃጠሎ ህይወቱ ሲያልፍ፤ ሁለቱ ደግሞ ህንፃው ውስጥ መሞታቸው ተገልጿ። ህንፃው ላይ ይሰሩ የነበሩ 13 ሰዎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
• አውሎ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ የጃፓን ዋንኛ አውሮፕላን ማረፊያ ተዘጋ። አውሮፕላን ማረፊያው የተዘጋው ከከተማ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ በመደርመሱ ነው። በአውሮፕላን ማረፊያው ችግር ውስጥ የወደቁ መንገደኞች በመርከብ እንዲጓጓዙ ተደርጓል።
• አፍሪካ አሜሪካዊቷ በአሜሪካ ምክር ቤት የዲሞክራቶች የማሳቹሴትስ ተወካይ ሆነው ተመረጡ። አያና ፕረሲሊ ለዚህ ሃላፊነት የበቁ የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊ ሴት ናቸው ተብሏል።