ባቡር ውስጥ ወንበርዎን ለማን ይለቃሉ?

ልጇን ቆማ ለማጥባት ተገዳለች

የፎቶው ባለመብት, Instagram/Hitchens' Kitchen BLW Club

የምስሉ መግለጫ,

ልጇን ቆማ ለማጥባት የተገደደችው እናት

ልጅ የታቀፈች ሴት ባቡር ውስጥ ቢመለከቱ መቀመጫዎን ይለቁላታል? የብዙዎች ምላሽ "መጠርጠሩስ" ሊሆን ይችላል። ከወደ እንግሊዝ የተሰማው ዜና ግን አጀብ ያስብላል።

ኬት ሂቸንስ 32 ዓመቷ ነው። ከለንደን ወደ ዊክፎርድ ለመሄድ ባቡር ተሳፍራ ነበር።

የስድስት ወር ልጇን ታቅፋ ባቡር ውስጥ ስትገባ ሁሉም መቀመጫዎች ተይዘው ነበር። አይኗ ወዲያ ወዲህ ቢያማትርም ወንበሩን ሊለቅላት የሚፈቅድ አላገኘችም።

ልጇን ማጥባት ስትጀምርም ማንም አልተነሳላትም። ተሳፋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የባቡሩ ላይ ሰራተኞችም አልተባበሯትም።

ተሳፍራበት የነበረበት ባቡር ሶስት ጣቢያዎች ላይ ቆሟል። ሆናም በሶስቱም ጣቢያ አንድም ሰው እንኳን ከወንበሩ አልተነሳላትም።

ሁኔታው ያበሳጫት ጦማሪቷ ኬት፤ ፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ "መልካም ብንሆን ምናለበት?" የሚል መልእክት አስተላልፋለች።

ወንበር ልቀቁልኝ ብላ መጠየቅ ብትችልም፤ ተሳፋሪዎቹ ሳትጠይቅ በፊት ወንበር እንደሚያሻት መገንዘብ እንደነበረባቸው ትናገራለች።

አንዲት እናት እንቅስቃሴ ላይ ያለ ባቡር እየናጣት፣ ልጇን በክንዷ አስደግፋ ለማጥባት ስትጣጣር እያዩ ምንም እርዳታ ለመስጠት የማይሞክሩ ሰዎችን መመልከት "አለማችን ወዴት እየሄደች ነው?" የሚል ጥያቄ እንድታነሳም አስገድዷታል።