የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ኤጄንሲ ሊቋቋም ነው

ቃል-አቀባይ መለስ አለም

የፎቶው ባለመብት, MoFA

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ አንድ ማለዳ በሰጡት መደበኛ መግለጫቸው እንደተናገሩት በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ እንዲሁም ወደ አገር ቤት እየተመለሱ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ አተኩሮ የሚሰራ የዲያስፖራ ኤጄንሲ ለማቋቋም ሥራ ተጀምሯል።

ኤጄንሲው ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የማስተባበር፣ ባሉበት አገር ተጠቃሚነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፤ እንዲሁም ለአገር የሚያደርጉትን አስተዋፅዖ ከፍ እንዲል ሥራዎችን የመስራት ኃላፊነት ይኖረዋል ሲሉ አቶ መለስ ገልፀዋል።

ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ የሚያደርገው ተቋሙ ከተቀዳሚ ግቦቹ መካከል በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መብቶች እና ሰብዓዊ ክብሮች ማስጠበቅ ነውም ተብሏል። የኢትዮጵያዊያኑን ተሳትፎ ማረጋገጥ ደግሞ ሌላኛው ዓላማው ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት በዳይሬክቶሬት ፅህፈት ቤት ደረጃ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከቱ ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ቢሆንም እስካሁን የነበረው አሰራር እና አደረጃጀት የነበሩት ውስንነቶች ለመቅረፍ እንዲሁም ዲያስፖራው በአገር እድገት ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን እምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ኤጄንሲውን ለማቋቋም መወሰኑን ነው ቃል አቀባዩ ያስረዱት።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ "ከሌላ ሥራ ጋር ተለጥፎ የሚሰራ ተደራቢ ሥራ ሊሆን አይገባም" ብለዋል አቶ መለስ።ከአስራ አምስት ዓመት በፊት 130 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተልኮ እንደነበር ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ይህ የገንዘብ መጠን 5 ቢሊየን ዶላር ቢደርስም፤ አብዛኛው ገንዘብ በኢመደበኛ መንገዶች የሚላክ መሆኑ ዓይነተኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

"ዜጎቻችን በየአገሩ ካሉ ሚሲዮኖቻችን ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጎ አልነበረም። በሚሲዮኖቻችንም የአቅም ውስንኑነት አለ" ያሉት አቶ መለስ ይህም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ቁጥር በተመለከተ ግምቶችን ከልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለመውሰድ ግድ መሆኑን ገልፀው አሁን በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሦስት ሚሊዮን የሚገመት እንደሆነ ተናገረዋል።

"ዲያስፖራው በአገሩ ላይ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ የፖለቲካ አመለካከት መመዘኛ መሆን የለበትም።"

እንደ አቶ መለስ ገለፃ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኤጄንሲውን መመሥረት ያፀደቀው ሲሆን በህግ አግባብ የማቋቋም ሒደቱ በመከናወን ላይ ነው።

ቃል አቀባዩ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሁለተኛ ጊዜ በኤርትራ እያደረጉት ያለው ጉብኝት ቀደም ሲል የተመሰረተው ግንኙነት እና የተደረሰበት ስምምነት ወደተግባር መተርጎም ምልክት ነው ብለዋል።

በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መሪዎች በአስመራ እየተካሄደ ያለውን የሦስትዮሽ ውይይት እና የስምምነት ፊርማ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ፤ ቀጣናዊ ውህደት ማምጣት የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ተናገረው ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳይ ለመናገር ግን የልዑካን ቡድኑን ወደ አገር ውስጥ መመለስ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።አቶ መለስ "በይቅርታ እንሻገር፣ በፍቅር እንደመር፤ ዲፕሎማሲያዊ ድልም እናስመዝግብ" በሚል ርዕስ ነው የዓመቱን የመጨረሻ መግለጫ የሰጡት።