ጂቡቲና ኤርትራን ለማስማማት ጥረት ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega/ Twitter
የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራትና በኤርትራና በጂቡቲ መካከል ቆየውን አለመግባባት መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተስማሙ።
የሦስቱ ሃገራት መሪዎች አሥመራ ውስጥ ባደረጉት ውይይትና በደረሱት ስምምነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በማህበራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም የቀጣናው አንድ አካል በሆነችው በጂቡቲና በኤርትራ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው የድንበር ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ ለማስቻል እንደሚጥሩም ተስማምተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከጅቡቲ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ወደ ጂቡቲ ተጉዘዋል።
በተያያዘ ዜና ኤርትራ በኢትዮጵያ የነበራትን ኤምባሲ ከከፈተች ከአንድ ወር በላይ በዝግጅት ላይ የቆየችው ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በአሥመራ ዛሬ ከፈተች።
ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሃያ ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት በማሻሻል የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በየሃገራቱ ደማቅ የሚባል ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ኤርትራ በቀዳሚነት ተዘግቶ የቆየውን የአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ሃምሌ አጋማሽ ላይ መክፈቷ ይታወሳል።
አሥመራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መልሶ ሲከፈት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማን በጋራ መስቀላቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
ትናንት ወደ ኤርትራ ተጉዘው በአሰብና ምፅዋ ወደቦች ላይ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከኤርትራና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር ውይይት ከማድረጋቸው ባሻገር የሦስትዮሽ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ ከትናንት ጀምሮ በኤርትራ ጉብኝት ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ዛሬ ረፋድ ላይ ከአሥመራ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።