የሐሙስ ምሽት አጫጭር ዜናዎች

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲከፈት

የፎቶው ባለመብት, FBC

ኢትዮጵያ

ቻይና ከዚያም ወደ ኤርትራ አምርተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጉዟቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቻይና እና በኤርትራ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ ተናግረዋል። ከቻይና በተገኘ ብድር የተገነባው የኢትዮ ጂቡቱ የባቡር መስመር የብድር መክፈያ ጊዜ ከ10 ዓመት ወደ 30 ዓመት ከፍ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የብድር አሰጣጥ ላይ ማሻሻያዎቸን ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን እና መስማማታቸውን ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታ በአስመራ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን ከፍተዋል።

ጅቡቲ

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ አገራቸው ከኤርትራ ጋር እርቀ-ሰላም ለማውረድ ዝግጁ መሆኗን መግለፃቸውን የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

ደቡብ ሱዳን

አስር የደቡብ ሱዳን ወታደሮች የእርዳታ ሰራተኞችን በመድፈርና በጋዜጠኛ ግድያ ተፈረደባቸው። ወታደሮቹ የተፈረደባቸው ከሰባት አመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት ነው። ተጎጂዎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው የአራት ሺህ ዶላር ካሳ እንዲያገኙ ተወስኗል።

ቻይናዊው በኬንያ

የዘረኝነት ስድቦች የሰነዘረውን ቻይናዊ ባለሃብት ኬንያ ልታባርር ነው። ይህ የሆነው ግለሰቡ ከሰራተኛው ጋር በተጋጨበት ቅፅበት "ኡሁሩ ኬንያታና ሌሎች ኬንያዊያን ጦጣ፣ ድሃና ጅላጅል ናቸው" ሲል የሚያሳየይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት መታየቱን ተከትሎ ነው። ቀደም ሲል ቻይናዎች በገነቡት የባቡር መስመር ላይ የሚሰሩ ኬንያዊያን በቻይናዊያን የዘረኝነት ጥቃት እየተፈፀመባቸው መሆኑን አስታውቀው ነበር።

ጃፓን

በሰሜናዊ ጃፓን በመሬት መንቀጥቀጥና መሬት መንሸራተት ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን የማውጣት ጥረት እንደቀጠለ ነው። በጃፓኗ ሆካይዶ ደሴት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም። የጃፓን ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በቀጣዩ ሳምንትም አካባቢው ተመሳሳይ ጥንካሬ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ሊመታ እንደሚችል አስታውቋል።

እንግሊዝ

እንግሊዝ ውስጥ በቀድሞ የሩሲያ ሰላይና ልጃቸው ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት ጀርባ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን በመሆናቸው ተጣያቂ መሆን አለባቸው ሲሉ የእንግሊዝ ደህንነት ሚኒስትር ቤን ዋላስ ተናገሩ። ሩሲያ ግን ተቀባይነት የሌለው በማለት ውንጀላውን አጣጥላዋለች።

አውስትራሊያ

በጫማዋ ሂል ኮኬይን የተባለውን የተከለከለ እፅ ልታስገባ ስትል ሲድኒ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተያዘችው አሜሪካዊት ሰባት ዓመት ተኩል ተፈረደባት። የሃምሳ አንድ ዓመቷ ሴት ነገሩ እሷ ያደረገቸው ሳይሆን ሳታውቀው በህገወጥ እፅ አዘዋዋሪዎች የተደረገ ነው ብትልም፤ ፍርድ ቤቱ ይህን መከላከያ ሳይቀበለው ቀርቷል።

አሜሪካ

የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከመቶ የሚበልጡ አገራት ላይ ከተሰነዘረው የበይነ መረብ (ሳይበር) ጥቃት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰሜን ኮሪያዊያንን ሊከስ ነው። በሳይበር ጥቃቱ በተለያዩ አገራት ሶስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ኮምፒተሮች የተጎዱ ሲሆን፤ ጥቃቱ በቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራን አስከትሏል።