"ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እራሳቸውን አጥፍተዋል"፤ ፖሊስ

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ

ሐሙስ ሐምሌ 19፣ 2010 ዓ. ም. መሃል አዲስ አበባ በሚገኘው መስቀል አደባባይ ጠዋት ላይ መኪናቸው ውስጥ በጥይት ሕይወታቸው አልፎ የተገኙት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እራሳቸውን እንዳጠፉ ፖሊስ በምርመራው እንደደረሰበት አሳወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄነራልና ምርመራውን ያከናወኑ የፖሊስ አባላት በተገኙበት ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ መኪናቸው ውስጥ የተገኘው ሽጉጥ የኢንጂነሩ እንደነበር ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄነራል ዘይኑ ጀማል እንዳሉት የመጀመሪያው የምርመራው ውጤት ኢንጂነሩ በሌላ ሰው እጅ እንዳልተገደሉ ያሳያል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው ከመሞታቸው ቀደም ብሎ በነበረው ዕለት ከትልቁ ልጃቸው ጋር የስንብት የሚመስል መልዕክት ይለዋወጡ እንደነበር ፖሊስ በመግለጫው አመልክቷል።

ኢንጅነሩ ከመሞታቸው በፊት ባደረጉት የስልክ ልውውጥም የስንብት ይዘት ያለው መልዕክት ከፀሃፊያቸው ጋር ተለዋውጠዋል ተብሏል። በተለይ ለፀሃፊያቸው የልጃቸውን ነገር አደራ በማለት መልክዕክት ማስተላለፋቸውን የፌደራል ፖሊስ ጀኔራል ኮሚሽነር ዘይኑ ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ባለፈበት እለት ጠዋት ላይም ለሾፌራቸው ፖስታ በመስጠት ለማን እንደሚያደርስላቸው "እነግርሃለው" ማለታቸውና ለሌላኛው ሾፌር ደግሞ ለመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሚደርስ ፖስታ መስጠታቸው ተጠቅሷል።

ኢንጂኒየሩ ከመሞታቸው በፊት ማስታወሻቸው ላይ ለሞታቸው ምክንያት ሊሆን የሚችል አመላካች መረጃ አለመገኘቱንም ፖሊስ ገልጿል።

መኪናቸው ውስጥ የተገኙት ደብዳቤዎችና ማስታወሻዎች በአብዛኛው የሚያሳዩት ከእለት ተለት ሥራቸው ጋር የሚያያዙ መልዕክቶችን እንጂ ሞታቸውን የተመለከቱ እንዳለሆነ ፖሊስ አመልክቷል።

የኢንጂነሩን ሞት በተመለከተ ፖሊስ የደረሰበትን ውጤት በአቃቤ ሕግ በኩል ይፋ እንደሚደረግ ሁለት ጊዜ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ወደ ሌላ ቀን ተላልፎ ነበር።

ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው፤ የአሜሪካ ፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) አባላት የኢንጂነሩ ሕይወት ከጠፋበትን ሽጉጥ ጋር የተያያዘ ምርመራ ላይ አስተዋፅኦ ነበራቸው ተብሏል።

ኢንጅነር ስመኘው ሞተው የተገኙበት ደብዛዛ ወርቃማ ቀለም ያለውና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 ኢቲ ኤ29722 የሆነው ላንድ ክሩዘር ቪ8 መኪናቸው፤ ቀን ከሌት እንቅስቃሴ በማይጠፋውና ጥበቃ በማይለየው መስቀል አደባባይ መገኘቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

የፌደራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄነራል ዘይኑ እንዳሉት ኢንጅነሩ ሞተው የተገኙበት መኪና ሞተሩ ሳይጠፋ አራቱም በሮቹ ተቆልፈው ነበር። በጄነራሉ ገለጻ መሰረት፤ የመኪናው አሰራር መኪናው ሞተሩ ሳይጠፋ ከውስጥ ለመቆለፍ አያስችልም። ስለዚህም ኢንጅነሩ መኪናው ውስጥ ሳሉ እንደቆለፉት ያሳያል ብለዋል።

ፖሊስ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በታቀደው ፍጥነት ሳይሄድ መጓተቱ ለኢንጂነሩ ሞት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ያለውን ግምት በመግለጫው ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከሞታቸው ጀርባ ያሉ ጉዳዮችን የምርመራ ቡድኑ እያጣራ መሆኑን ጠቅሶ፤ ሙያዊ በሆነ መንገድ የሚካሄደው ምርመራ እንደተጠናቀቀም ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ ይሆናሉ ብሏል።

በተጨማሪም በኢንጂነር ስመኘው በቀለ የቀብር ሥነ ስርዓት ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው ተፈጽሟል የተባለው ዝርፊያም ተራ የሚባል የስርቆት ድርጊት መሆኑንም ፖሊስ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ዝርፊያው ድርጊትም በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ከውጭ ሃገር የመጡ ዘመዶቻቸው ንብረት በተቀመጠበት ክፍል ላይ ማጋጠሙንና ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከኢንጂነሩ ሞት ቀደም ብለው የግድቡ ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑና በዚህ አካሄድ ከቀጠለም በአስር ዓመታት ውስጥ እንደማይጠናቀቅ ስጋታቸውን ገልፀው ነበር።

ኢንጂነር ስመኘው ከህልፈታቸው አንድ ቀን በፊት ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፕሮጀክቱን ሂደት በግንባታው ቦታ ተገኝተን እንድንመለከት ጋብዘውን ነበር።