ወጣቱ እራሱን 'ሰልፊ' ሲያነሳ ህይወቱ አለፈ

በዮዝማይት ብሄራዊ ፓርክ ጎብኚዎች ሲራመዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ይህን ፓርክ በየዓመቱ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ይጎበኙታል

አንድ እስራኤላዊ ወጣት በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ዮዝማይት ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ እራሱን ፎቶ እያነሳ ሳለ ነው ይህ አሳዛኝ ክስተት የተፈጠረው።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ቶመር ፍራንክፉተር የ18 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ለጉብኝት ብሎ ነበር የሁለት ወራት ቆይታውን በአሜሪካ ለማድረግ ከሃገሩ የወጣው።

የወጣቱ እናት እንደተናገሩት ልጃቸው አሜሪካ በሚገኘው ፓርክ ውስጥ እራሱን ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር 250 ሜትር ከፍታ ካለው ጉብታ ላይ ወድቆ ህይወቱ አልፏል።

የወጣቱን የቀብር ስነ ስርአት ለመፈጸም ሬሳውን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።

ባለፈው ሰኔ ወር በዚሁ ፓርክ ሁለት የተራራ አድናቂዎች የአካባቢውን ተፈጥሯዊ አሰራር ለመመልከት ወደ ተራራው ጫፍ ሲወጡ ወድቀው ሁለቱም ህይወታቸው አልፏል።

ከዚህ በተጨማሪ ከባለፈው ዓመት ጀመሮ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በፓርኩ ውስጥ ከተራራ ላይ ከመውደቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ዮዝማይት ብሄራዊ ፓርክ በካሊፎርያ ግዛት ባጋጠመው ከባድ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ተዘግቶ የቆየ ሲሆን፤ ለጎብኚዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው በቅርቡ ነው።