ኤች አይ ቪን የሚከላከለው መድሃኒት ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ

የኤች አይ ቪ መከላከያ መድሃኒት

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ዌልስ ውስጥ በሙከራ ደረጃ የሚገኘው የኤች አይ ቪ መከላከያ መድሃኒት ለማግኘት የሚደረገው ምርምር በበሽታው የመያዝ እድልን ለመቀነስ ሊረዳ እንደሚችል እየተገለጸ ነው።

የመድሃኒቱን ውጤታማነት ለመፈተሽ ለበሽታው የመጋለጥ ከፍተኛ እድል አላቸው ለተባሉ 559 የሙከራ ጥናቱ ተሳታፊዎች ከለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ መድሃኒቱ መስጠት የተጀመረ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ሁሉም ሰዎች ኤች አይ ቪ አልተገኘባቸውም።

ይህም ውጤት እጅግ አስደሳችና በበሽታው ዙሪያ ያሉ መጠራጠሮችን የሚቀንስ ነው ተብሎለታል።

ምርምሩን የሚያካሂዱት የህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ላይ ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች እንደተገኙባቸውና ከኤች አይ ቪ ነጻ መሆናቸው ደግሞ የመድሃኒቱን ውጤታማነት ያሚያሳይ ነው።

መድሃኒቱ ''ፕሪ ኤክስፖዠር ፐሮፊላክሲስ'' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በየቀኑ የሚወሰድ ሲሆን በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ የመተላለፍ እድሉን እስከ 86 በመቶ ድረስ ይቀንሳል ተብሏል።

እስካሁን ድረስ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩና ሌሎች ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ ነን ብለው የሚያስቡ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና ፈረንሳይ የሚገኙ ሰዎች መድሃኒቱን መጠቀም ጀምረዋል።