የአርብ ምሽት አጫጭር ዜናዎች

ሮበርት ሙጋቤና ግሬስ ሙጋቤ

ዙምባብዌ

ሃምሌ ላይ ከተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ይፋዊ ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የኤመርሰን ምናንጋግዋን በምርጫ ማሸነፍ እንደሚቀበሉት ገለፁ።

ከዚህ ቀደም በህገወጥ መንገድ ከስልጣኔ አስወግደውኛል በማለት ሙጋቤ ድምፃቸውን ለምናንጋግዋ እንደማይሰጡ አስታውቀው ነበር።

የሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤም የምናንጋግዋ የአገሪቱ መሪ መሆን የፈጣሪ ፍቃድ ነው ብለዋል።

ጥንዶቹ ይህን የተናገሩት ባለፈው ሳምንት የሞቱት የግሬስ እናት የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ነበር።

ዙምባብዌ

የዚምባብዌ ጤና ጥበቃ ባለስልጣናት በአገሪቱ መዲና ሃራሬ ኮሌራ መቀስቀሱንና እስካሁንም አንድ ሰው መሞቱን አስታውቀዋል።

የሌሎች አራት ሰዎች ሞትም እየተጣራ ሲሆን ምልክቱ የታየባቸው ሰላሳ ሰዎችም ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ወረርሽኙ እንዴት ተቀሰቀሰ የሚለውም በመጣራት ላይ ነው።

ከአስር አመት በፊት በአገሪቱ በኮሌራ ወረርሽኝ መቶ ሺህ የሚሆኑ ሲታመሙ አራት ሺህ ሞተዋል።

ላይቤሪያ

ፈረንሳይ እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ የላይቤሪያ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ጦርነት የታጣቂ ቡድን ኮማንደር ነበር ያለችውን ግለሰብ አሰረች።

ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት ዜግነቱ ኔዘርላንዳዊ ሲሆን ሰብአዊነትን በመጣስ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

ግለሰቡ ሰዎችን በማሰቃየት ፣ በግድያ ፣ ህፃናትን በውትድርና በማሰማራት ፣ሰዎችን ባሪያ በማድረግና በሌሎችም ወንጀሎች ተጠርጥረዋል።

በጦርነቱ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ሲገደሉ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተሰድደዋል።

ማሊ

እንደ አውሮፓውያኑ በዚህ ዓመት በሰሜንና ማእከላዊ ማሊ ሃምሳ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በግጭት እንደተፈናቀሉ አንድ የኖርዌ እርዳታ ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ግጭቶችም በተደጋጋሚ ይቀሰቀሳሉ።

በአካባቢዎቹ ፀረ አክራሪ ሚሊሻዎች ወታደራዊ ተልእኮዎችም ይፈፀማሉ።

የማሊ ግጭት ከተቀሰቀሰ ስድስት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት አምስት ሚሊዮን የአገሪቱ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ብሏል።

ሜክሲኮ

በሜክሲኮ ቬራክሩዝ በተሰኘ ከተማ በጅምላ የተቀበሩ 166 ሰዎች የራስ ቅል ተገኘ።

የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንደተናገሩት የሰዎቹ አፅም ቢያንስ እዚያ ቦታ ላይ ለሁለት ዓመት ተቀብሮ ቆይቷል።

ለጥንቃቄ ሲባል የመቃብሩ ልዩ ስፍራ ያልተገለፀ ሲሆን ሁለት መቶ የሚሆኑ ልብሶች፣ ከመቶ የሚበልጡ መታወቂያ ካርዶችና ሌሎች ቁሳቁሶች ከመቃብሩ ውስጥ እንደተገኙ ተገልጿል።

አሁንም የመቃብር ስፍራው ላይ በድሮንና በመሬት ሰንጣቂ ራዳር በመታገዝ ምርመራው እንደቀጠለ ነው።

ኤች አይ ቪ

በሙከራ ላይ የነበረ የኤች አይ ቪ መከላከያ መድሃኒት ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይቷል ተባለ።

በእንግሊዝ አገር የሚገኝ ክሊኒክ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መድሃኒቱን እንዲወስዱ በማድረግ እንደ አውሮፓውያኑ ሙከራውን የጀመረው ባለፈው ነበር።

በዚህም አምስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሰዎች መድሃኒቱን እንዲወስዱ ተደርጎ የነበረ ሲሆን እስካሁን አንዳቸውም ለቫይረሱ አልተጋለጡም ተብሏል።

ጣልያን

ጣልያን ስደተኞችን ሲረዱ ነበር የተባሉ ቱኒዚያዊ አሳ አጥማጆችን ማሰሯ ቁጣ ቀስቅሷል።

ጣልያን በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጠርጥራ ያሰረቻቸውን ስድስት ቱኒዚያዊያንን እንድትለቅቅ ቱኒዚያዊያን ጠይቀዋል።

ብራዚል

በብራዚል ምርጫ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሆኑት ጄር ቦልሶናሮ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በስለት ተወጉ።

ህዝብ በተሰበሰበበት በስለት የተወጉት ተወዳዳሪው ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸዋል።

ዘረኝነትን በሚያንፀባርቁ ንግግሮቻቸው ብዙዎችን የሚያበሳጩት ተወዳዳሪው በትንበያ ድምፅ ማሰባሰብ ጥሩ ውጤት አግኝተው ነበር ተብሏል።

ቦልሶናሮ በሆስፒታል በለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስል የግድያ ሙከራ ይደረግብኛል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ቀዶ ህክምና ካደረጉላቸው ዶክተሮች አንደኛው ቀዶ ህክምናቸው ረዥም ሰዓታት እንደወሰደ ተናግረዋል።

እንግሊዝ

የቀድሞ የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከባለቤታቸው ጋር ተለያዩ።

ጥንዶቹ ከሃያ አምስት ዓመት አብሮነት በኋላ ለመለያየት መወሰናቸውንና የፍቺያቸው ሂደት መጀመሩንም ተናግረዋል።