በደቡብ ሱዳን አውሮፕላን ተከስክሶ '19 ሰዎች ሞቱ'

በደቡብ ሱዳን አውሮፕላን ተከስክሶ '19 ሰዎች ሞቱ'

በደቡብ ሱዳን አንድ አነስተኛ አውሮፕላን በደመናማ የአየር ሁኔታው ውስጥ ለማረፍ ስትሞክር ሃይቅ ላይ ተከስክሳ 19 ሰዎች ሞቱ።

ከአደጋው አራት ሰዎች ብቻ የተረፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ህጻናት መሆናቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ከሟቾቹ መካከል ዋና እና ምክትል አብራሪ እንዲሁም የቀይ መስቀል ባልደረባ እንደሚገኙበት የአካባቢው ባለስልጣናት ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

23 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችው አውሮፕላን እሁድ ዕለት ከደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ዪሮል ወደሚባል ሥፍራ እያመራች ነበር።

''ዪሮል ስትደርስ የአየር ጸባዩ ደመናማ ነበር። ለማረፍ ስትሞክር ዪሮል ሃይቅ ላይ ተከሰከሰች'' ሲሉ የቀጠናው የመንግሥት ባለስልጣን አቤል አጉኤክ ተናግረዋል።

''ሙሉ የከተማው ህዝብ ተደናግጧል፤ ሱቆች በሙሉ ዝግ ናቸው። ወዳጅ ዘመዶች የተጎጂዎችን አስክሬን ተረክበዋል። የተከሰከሰው የንግድ አውሮፕላን ነው'' በማለት አቤል አክለዋል።

አውሮፕላኗ ስትከሰከስ በአካባቢው የነበሩ አሳ አስጋሪዎች በታንኳ በመታገዝ ከአደጋው ህይወታቸው የተረፉትን ለማደን ሲጥሩ ታይተዋል።