በማዳጋስካር ስታድየም ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

በማዳጋስካር ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

ማዳጋስካር እና ሴኔጋል የነበራቸውን የእግር ኳስ ግጥሚያ ለመከታተል በማዳጋስካር ስታድየም ተገኝተው የነበሩ ታዳሚያን ያላሰቡት ገጥሟቸዋል።

ከጨዋታው ጅማሬ በፊት በተከሰተው ግርግር ምክንያት አንድ ሰው ተረጋግጦ ሲሞት አርባ ያክል ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አንደኛው መግቢያ በር ብቻ ክፍት የተደረገው ስታድየም ከአቅሙ በላይ ሰው ማስተናገዱ ለአደጋው እንደ ምክንያት እየተጠቀሰ ነው።

ጉዳት ደርሶባቸው በርዕሰ መዲናዋ አንታናናሪቮ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እርዳታ በማግኘት ላይ ካሉ መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑም ተሰምቷል።

ቁጥራቸው የትየለሌ የሆኑ የእግር ኳስ ወዳጆች ጨዋታውን ለመታደም ከንጋት ጀምሮ ሰልፍ ይዘው ሲጠባበቁ ነበር።

የስታድየሙ በር ሲከፈት ተመልካቾች በግርታ ወደ ውስጥ መግባት ጀመሩ ሲል አርኤፍአይ የተሰኘው የፈረንሳይ ራድዮ ጣብያ ሁኔታውን ዘግቦታል።

«ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ ይዘን ስንጠብቅ ነበር፤ ግርግሩ ሲጀመር ከመግቢያ በሩ ቅርብ ርቀት ላይ ነበርን» ሲል ሪቮ የተባለ ግለሰበብ ክስተቱን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል አስረድቷል።

«ይህን ለመሰለ ትልቅ ጨዋታ የስታድየሙን አንድ መግቢያ በር ብቻ መክፈት ለምን እንዳስፈለገ ነው ያልገባ» ያለው ደግሞ ሃሪዛፍ የተባለ ሰው ነው።

የሊቨርፑሉ ኮከብ ሳድዮ ማኔ ጨምሮ ሌሎች ተወዳጅ ተጫዋቾችን ለመመልከት ወደ ስታድየም የዘለቁት ማዳጋስካሪዎች ያልጠበቁት ገጥሟቸዋል።

ጨዋታው 2 - 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአንጎላ ተመሳሳይ ክስተት ተከስቶ 17 ሰዎች መሞታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

በማላዊም ተመሳሳይ ግርግር የስምንት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ነው።