2010 ያልተጠበቁና ተደራራቢ ክስተቶች የታዩበት ዓመት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ለውጥ

ተሰናባቹ 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በፋታ አልባ ድርጊቶች የተሞላ እንዲሁም ከፍተኛ ለውጦችን ያግተለተለ እንደነበር መስማማት ይቻላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀውበታል፣ ሦስት ዓመት ባለሞላ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ ታውጆበታል፣ የቆይታ ጊዜውን ሳያጠናቅቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶበታል።

በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ፊታውራሪነት ከቀደሟቸው ሁለት መሪዎች በአቀራረብም በአቋምም እንደሚለዩ የተነገረላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ገብተው ተሰይመውበታል።

በተለያዩ የስልጣኖች መንበሮች በርካታ ዓመታትን ተቀምጠው የቆዩ ጎምቱ ሹማምንቶች ተሰናብተውበታል፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ እና ከፖለቲካ ተሳትፎ ወይንም አቋማቸው ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ የተነገረላቸው ግለሰቦች የወህኒ አጥሮችን ለቀው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ተቀላቅለውበታል፤ ጥቂት በማይባሉ ማረሚያ ቤቶች ሲፈፀሙ የከረሙ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች ወደ ህዝብ ዓይኖች እና ጆሮዎች ደርሰውበታል።

ኢህአዴግ እና በውስጡ ያቀፋቸው አራት ፓርቲዎች ላዕላይ አመራሮች የሚያልቁ በማይመስሉ ተከታታይ ጉባዔዎች ተጠምደውበት ባጅተዋል፤ ክልሎች (ትግራይ፣ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ ሶማሌ) እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መራኄ መንግሥታቶቻቸውን ቀይረውበታል፤ የገዥው ፓርቲ የውስጥ ሽኩቻ ማስተባበል የማይቻልበት ደረጃ ደርሶበታል፤ የክልል ፕሬዚዳንት ከስልጣናቸው ወርደው ተወንጅለውበታል።

አራቱ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ምስላቸውን ለመቀየር ተውተርትረውበታል፤ ገሚሶቹ ሹማምንትን ከመለዋወጥም በዘለለ ስምና አርማቸውን በአዲስ ለመተካት እስከመዳዳት ደርሰዋል።

ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ አምደኞች እና ጸሐፍት በቅርብ ዓመታት ከለመዱት መሳደድ እና መታፈን መላቀቅ ይሰማቸው እንደያዘ ብስራት ተናግረውበታል።

የተዘጉ ድረ ገፆች ተከፍተውበታል፤ ማንም ዜጋ እንዳይታደማቸው መንግሥታዊ የተዓቅቦ ድንጋጌ ታውጆባቸው የነበሩ የብዙኃን መገናኛዎች ነፃ ተለቅቀውበታል፤ ውጭ የነበሩ ወደ አገር ቤት ተመልሰውበታል፤ ጽሕፈት ቤት ከፍተውበታል።

የፖለቲካ መሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የሕዝባዊ ንቅናቄ አሿሪዎች እና አስተባባሪዎችም እንዲሁ ወደ አገር ቤት ተመልሰውበታል፤ ደጋፊዎቻቸው ወትሮ የሚያስወነጅሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን ይዘው ተቀብለዋቸዋል።

የተቃውሞ ቡድኖች ከሽብር መዝገብ ላይ ስማቸው ተሰርዞበታል፤ እነርሱም በፋንታቸው የነፍጥ ትግል በቃን ብለው አውጀውበታል፤ የሽብር ሕጉን ጨምሮ ሌሎችም አፋኝ ናቸው የተባሉ ሕግጋት ማሻሻያ ሊደርግባቸው ሽር ጉድ መጀመሩ ተግልፆበታል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ዐብይ አህመድ፡ ያለፉት 100 ቀናት በቁጥር

የፖለቲካ ገው ገጭ መብዛት ምጣኔ ኃብቱ ላይ ጫና መፍጠሩ ተነግሮበታል፤ ለግሉ ዘርፍ ተከርችመው የቆዩ መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች ለሽያጭ በራቸውን ሊከፍቱ ተሰናድተውበታል፤ በየዘርፉ በርካታ ኮሚቴዎች እና ቦርዶች ተቋቁመውበታል።

ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት ፀንቶ የቆየው ጠላትነት ተደምድሞ አዲስ ወዳጅነት ተኮትኩቶበታል፤ ከሌሎችም የቀጠናው አገራት ጋር ትስስር ሲጠነክር ተስተውሎበታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሒደት የተሰነቀረበት ቅርቃር ግልጥልጥ ያለ መስሎበታል፤ የግንባታው መሪ በመዲናይቱ ዋና አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተውበታል፤ ፖሊስ በምርመራየ ራሳቸውን እንደገደሉ ተገንዝቤያለሁ ቢልም በዚህ ድምዳሜ ላይ ሕዝባዊ መከፋፈል ጎልቶ ታይቷል።

አገሪቱ በተጋነነ ተፈጥሯዊ አደጋ ባትላጋም፤ በዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎችን ያፈናቀሉ ብሔር ተኮር ግጭቶች በየስፍራው ተለኩሰዋል፣ ተጋግለዋል፤ ተፈናቃዮቹን የማስፈር እና/ወይንም ወደቀደመ ቀያቸው የመመለስ ፈተና የመንግሥት ጫንቃ ላይ ወድቆበታል።

ሁለቱ ትልልቅ የአገሪቱ ኃይማኖቶች የኦርቶዶክስ ክርስትና እና እስልምና በመሪዎቻቸው መካከል የነበሩ ቁርሾዎች ረግበውበታል፤ ወደ እርቅም ተጉዘውበታል።

እንዲያም ሆኖ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የሰርክ ክስተት እስኪመስሉ ተደጋግመውበታል፤ ብሔረተኛነት ይበልጥ ሥር የሰደደ መስሏል። የፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ፉክክሮች ባንዲራን በመሳሰሉ ትዕምርቶች ላይ ከርረውበታል።

እነዚህ ሁሉ ክስተቶች የማሰቢያ እልባት እንኳ በማይሰጥ ፍጥነት ተግተልትለው መከወናቸው ቆም ብሎ ተራዛሚ ፋይዳቸውን ለመረዳት፣ አንድምታቸውን ለመገምገም እና አቅጣጫቸውን ለመተንበይ ዕድል የሚነፍግ መሆኑ አልቀረም።

ይሁንና 2010 በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መስክ ላይ በልዩነት ከሚጠቀሱ ዐበይት ዓመታት መካከል አንዱ ሆኖ ወደፊት መወሳቱ እንደማይቀር ምክንያታዊ የሆነ ግምት መስጠት ይቻላል።

ዓመቱ ጷጉሜ አምስት ቀን የቆይታ ጊዜውን ድምድሞ ለቀጣዩ ዱላውን ሲያቀብል ግን አብሮ የሚያስረክባቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች መኖራቸውም አይታበልም።

ኢህአዴግ አለ ወይ?

ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች ስትናጥ እና መንግሥትም እነዚህን ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር ሲውተረተር፥ ገዥውን ፓርቲ ባዋቀሩት አራት ብሔር ተኮር የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ነፋስ መግባቱ ግልፅ ይሆን ጀምሯል።

በተለይም ተቃውሞዎቹን ገንነው የነበሩባቸውን የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን የሚወክሉት የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ተቃውሞዎቹን ያፋፍማሉ በሚል ከገዛ ጠቅላይ ፓርቲያቸው እንዲሁም ከኢህአዴግ ጥምረት መስራች ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በይፋም ባይሆን በትችት ሲሸነቆጡ ይደመጥ ነበር።

ቆይቶም በተለይ ኦህዴድ ከገዥው ፓርቲ አባልነት ይልቅ ተቃዋሚ ፓርቲ እየመሰለ መጥቷል የሚሉ ተንታኞች አልጠፉም ነበር።

የኦህዴዱ ሊቀመንበር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግን አውራ ስልጣን የተቆናጠጡበት ሒደት እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላም ያስጀመሯቸው የለውጥ እና የማሻሻያ እርምጃዎች በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉትን ስንጥቃቶች ሲያጠቡ አልተስተዋሉም።

አሁን ያለውን የኢህአዴግ አሰላለፍ ለውጥ ደጋፊዎች እና ለውጡን ተቃዋሚዎች በሚል ጅምላ ክፍፍል መድቦ መናገር እየተለመደ ቢሆንም አራቱንም ፓርቲዎች የሚሻገር በአመለካከት ላይ ብቻ የተመሠረተ ምደባ ብቻ ከመምሰሉ ይልቅ ህወሓትን በአንድ ወገን ኦህዴድን፣ ብአዴንን እንዲሁም በርካታ ላዕላይ አመራሮቹን በዚሁ ዓመት የቀየረውን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕዝቦች ንቅናቄን (ደኢህዴን) በሌላ ወገን መለያነቱ የሚያይል ይመስላል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 100 የሥራ ቀናት በቁጥር ሲቀመጡ ምን ይመስላሉ?

በየፓርቲዎቹ ያሉት ነባር አመራሮች መገለላቸው፤ ኢህአዴግ በዐብይ አህመድ መሪነት ከያዛቸው አዳዲስ የአመለካከት መስመሮች ጋር ተዳምረው የወትሮ መልኩ በአያሌው በመቀየሩ የወትሮ ተቃዋሚዎቹ ሙገሳ ሲዘንብለት ትችት የሚሰነዘርበት በአብዛኛው ከቀድሞ አሞጋሾቹ ሆኗል።

የአራቱ ፓርቲዎች ግንኙነት ቀጣይ መልኮችን ጊዜ የሚገልጣቸው ቢሆንም ባለፈው መንፈቅ የታየው ኢህአዴግ በቀደሙት ሃያ ሰባት ዓመታት ከነበረው ኢህአዴግ ስሙ እና አርማው ሲቀሩ በብዙ መስፈሪያዎች የተለየ ቀለም እንዳለው መከራከር ይቻላል።

ፓርቲው በአንድ ወቅት ሊያደርገው ይችላል ሲባል እንደነበረው ከግንባርነት ወደ ውህደት ይሸጋገራል? ከአባል ፓርቲዎቹ መካከል የሚቀነሱ ይኖራሉ? የሚጨምራቸው ሌሎችስ? በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በአስተዳደራቸው ቃል የተገቡ የተቋማዊ እና ህጋዊ ማሻሻያዎች ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ በፓርቲው ቁመና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ? ጊዜ የሚመልሳቸው ጥያቄዎች ናቸው።

ቅራኔዎች እንዴት ይታረቁ?

በአጎራባች ወረዳዎች፣ ዞኖች እና ክልሎች መካከል ግጭቶች እየተከሰቱ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል።

በአንዳንድ ግጭቶች ወቅት የታዩ አሰቃቂ ጭካኔዎች የችግሩን አሳሳቢነት አጉልተው አሳይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ተጉዘው ነዋሪዎችን አነጋግረዋል፣ አመራሮችን ወቅሰዋል፣ ይህንን ተከትሎም ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ እንዲሁም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ሹማምንት አሉ።

በግጭቶቹ አለንጋ የተሸነቆጡ ብዙኃን ግን ህይወታቸው እንደተናወጠ ነው ዓመቱን የሚሰናበቱት፤ በልዩ ልዩ መስኮች መልካም ትልሞችን እንደመተረ የሚናገረው እና በበርካቶችም የሚመሰከርለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አስተዳደር ላይ ማዲያት የሚያስቀምጥ እውነታም ነው።

በዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነትን የሚቀፈድዱ እና ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች አዲስ ክስተት ባይሆኑም ከወትሮው በተለየ መደጋገማቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም እና የአብሮነት መልዕክቶች ጋር በቀጥታ የሚፃረሩ መሆናቸው ግልፅ ነው።

በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል ቁርሾ እየከረረ ሲሄድ የተስተዋል ሲሆን፤ ይህንንም ተግ ለማስባል በክልል መንግሥታቱም ሆነ በዜጎች መካከል የሚያመረቃ ሥራ ሲከናወን ታይቷል ማለት አይቻልም።

በሌላ በኩል መዲናዋ አዲስ አበባ ያለፉትን ሦስት ወራት በፈንጠዝያ ውቅያኖስ ተጥለቅልቃ ብታሳልፍም፤ በዚያውም ልክ የተፎካካሪ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችን ፍልሚያ ስታስተናግድ ቆይታለች።

ከስያሜዋ እስከሚውለበለቡባት ሰንደቅ ዓላማዎች ድረስ የመፃኢ ሙግቶችን አመላካች ቅድመ ጥቁምታ ሊባሉ የሚችሉ ሙግቶች በነቢብ ብቻም ሳይሆን በገቢር ተስተናግደውባታል።

ልዩ ልዩ አቋም ያላቸው፤ በተለያዩ የአደረጃጀት መንገዶች የተዋቀሩ በርካታ ፖለቲካዊ ቡድኖች ወደ አገር ቤት በአካልም በኃሳብም ሲመለሱ ይዘዋቸው የሚመጡ ተፋላሚ ምልከታዎችን ማስታረቅ ቀጣዩ ፈተና የሚሆን ይመስላል።

ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት የ2012 ዓ.ም የሚከናወነ ከሆነ ገዥውም ሆነ ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች ከመጪው ዓመት ቢያንስ የተወሰነውን ክፍል በዘመቻ እንደሚያሳልፉት መገመት ይቻላል።

ዘመቻዎቹ እነዚህን ቅራኔዎች ይብሱኑ አራግበዋቸው ውጥንቅጥ እንዳይፈጠር የሚሰጉ አካላት አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አስተዳደራቸው ይህንን ስጋት መቅረፍ ይችሉ ይሆን? የአገሪቱ ተቋማት እና ፖለቲካዊ ባህል የፍላጎቶችን ግጭት የማስተናገድ አቅም አዳብረዋል? ሌሎች የጊዜን መልስ የሚሽቱ ጥያቄዎች ናቸው።