"ምርጫ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም" ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ

በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ከመታሰቡ በፊት ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍን እንደሚገባ ትናንት የንቅናቄያቸውን አመራሮችና አባላትን በመምራት አዲስ አበባ የገቡት የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ምርጫና ውድድር ሳይሆን በሰከነ ሁኔታ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያጠናክር ሰላምና መረጋጋት በሃገሪቱ እንዲኖር ማድረግ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ምርጫ የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ ከማስቀመጥ በፊት ምርጫውን በተገቢው ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችሉና ሕብረተሰቡ የሚተማመንባቸው ተቋማትን በቀዳሚነት በተገቢው ቦታ ላይ መኖራቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

"ትኩረታችን መሆን ያለበት የተቀመጠን የምርጫ ጊዜን ማሳካት ላይ ሳይሆን፤ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስፈልጉት ተቋማትን እውን በማድረግ ላይ መሆን አለበት" ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

አሁን ኢትዮጵያ እያስተዳደረ ያለው መንግሥት ሃገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ከፍ ያለ ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ አሁን በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ሀገሪቱን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ከመሆን ውጭ ሌላ መደራሻ የለውም ሲሉም ብለዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ወደ ሰላማዊና ህጋዊ ፓርቲነት የመጣው በሀገሪቱ የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማጠናከርና የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት መሆኑን የድርጅቱ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልፀዋል።

በበርካታ ወጣቶች ባካሄዱት ትግልና መስዋፅትነት እንዲሁም በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች አሁን የተገኘው ለውጥ ያለው መዳረሻ አንድ መሆኑን ያመለከቱት ፐሮፌስር ብርሃኑ እሱም "ኢትዮጵያን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት ሃገር ማድረግ ነው" ብለዋል።

ለዚህም ሃገሪቱን ማረጋጋት ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበት አመልከተው፤ በማስከተልም ለዴሞክራሲያው ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ተቋማት የሚገነቡበት ጊዜ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ጨምረውም ለውጡ እውን እንዲሆን መስዋዕትነት ለከፈሉ መላው የሃገሪቱ ሕዝቦች ፤ እንዲሁም መብታችን ይከበር ብለው ባዶ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመብታቸው ታግለው ለተሰዉ ወጣቶችም ምስጋና አቅርበዋል።

በተመሳሳይም የሕዝቡን ትግል በመረዳት ከፍ ያላ ሃላፊነት በመውሰድ በኢህአዴግ ውስጥ የለውጥ ኃይል ለሆኑት እንዲሁም የእርቅና የአንድነት መንፈስን ላጠናከሩት የመንግሥት ባለስልጣናት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በቁጥር በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይዞ በተናጠል መንቀሳቀስ ለሕዝቡም ሆነ ለሃገሪቱ የሚኖረው ፋይዳ ጠቃሚ ስለማይሆን ፓርቲዎች በአመለካከት ከሚቀራረቧቸው ጋር እየተዋሃዱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሚመራው መንግሥት እንዲሁም ለለውጥ ከሚታገሉ ከየትኛው ወገኖች ጋር በትብብር ለመስራት ንቅናቄያቸው ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

መንቀሳቀሻውን ኤርትራ ውስጥ በማድረግ የትጥቅ ሲኣደርግ የቆየው የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት አዲስ አበባ በገቡበት ጊዜ በደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።