ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱ እስረኞች በይቅርታ ተለቀቁ

የመንግሥት መግለጫና የቤተሰብ ጥበቃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ክልሎች ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን በይቅርታ ለቀቁ።

ከክልሎቹ መስተዳደሮች የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጉዳያቸው በምህረት እንዲታይ የተወሰነላቸው እስረኞች ናቸው የአዲስ ዓመትን መምጣት ተከትሎ እንዲለቀቁ የተወሰነው።

በዚሁ መሰረትም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት 5325 እስረኞችን መልቀቁን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ጨምረውም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ እስረኞች በይቅርታ መለቀቃቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይም የአማራ ክልል ከ3 ሺህ ለሚበልጡ እስረኞች ይቅርታ ተደርጎላቸዋል። ይቅርታ የተደረገው የክልሉ ፍትህ ቢሮ የይቅርታ ቦርድ ታራሚዎቹ በይቅርታ እንዲፈቱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው።

ነገ የሚጀምረውን 2011 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ እስረኞችን ከለቀቁ ክልሎች መካከል የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ክልሎችም እንደሚገኙበት የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በዚሁ መሰረትም የጋምቤላ ክልል ከ370 በላይ እስረኞችን እንዲሁም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ 188 እስረኞችን በይቅርታ ከእስር መፍታታቸው ተገልጿል።