ድንበር ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከዛሬ ጀምሮ ለቀው ይወጣሉ

የኢትዮጵያ ወታደሮች በድንበር አካባቢ Image copyright AFP

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በኢትዯጵያና በኤርትራ ድንበር ላይ ለዓመታት ሰፍረው የነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከዛሬ ጀምሮ ለቀው መውጣት እንደሚጀምሩ አስታወቁ።

ይህ የሚሆነውም ከሃያ ዓመታት በኋላ ተዘግቶ የነበረው የሁለቱ አገራት ድንበር እንደገና ዛሬ መከፈቱን ተከትሎ ነው።

በድንበር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱን አገራት ወታደሮች ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁለቱም ሃገራት መሪዎቹን አጅበዋቸው ነበር። ዋነኛ የጦር ግንባር ሆነው ለሁለት አስርት ዓመታት በቆዩት የቡሬና የዛላምበሳ የድንበር አካባቢ መሪዎቹ ተገኝተው ነበር።

ኢትዮጵያና ኤርትራ፡ አዲስ ዓመትን በቡሬ ግንባር

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 20ኛ ዓመት - መቋጫ ያላገኘ ፍጥጫ

ከ1992 ዓ.ም ጦርነት በኋላ የሁለቱን አገራት ህዝቦች የሚያደርጉትን ንግድና እንቅስቃሴን ገትቶ የቆየውን ግንብ ትናንት የሁለቱ አገራት ወታደሮች መንገዶችን በመክፈት በድንበር ላይ ለእንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

በተባበሩት መንግሥት አሸማጋይነት በአውሮፓውያኑ 2000 የተደረገው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን መቆየት አገራቱን በባላንጣነት አቆይቷል።

ወታደሮችን ከድንበር አካባቢ እንዲለቁ ማድረግም የኤርትራ ዋነኛ ፍላጎቷ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በ2000 የተደረገውን የድንበር ኮሚሽኑን ጥሳለች ተብላ ተወቅሳበታለች።

አሁን ሁለቱም አገራት በቅርቡ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ከ1990ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበራቸውን ሁለቱን አገራት ግንኙነት በማይታመን መልኩ እየለወጠ ይገኛል።

የጊዜ ሠሌዳ

• ግንቦት 16/1985 ዓ.ም፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነፃ መውጣቷ በይፋ ታወጀ

• ሚያዚያ 28/90 ዓ.ም፡ የድንበር ጦርነቱ ተጀመረ

• ሰኔ 11/1992 ዓ.ም፡ ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ተፈረመ

• ታህሳስ 03/1993 ዓ.ም፡ የአልጀርስ የሰላም ስምምነት ተፈረመ

• ሚያዚያ 05/1994 ዓ.ም፡ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ይግባኝ የሌለውን ውሳኔውን አሳወቀ