"የመሰለህን ተናግሮ ከመኖር በላይ ጸጋ የለም" ዳንኤል ብርሃነ

የመጀመርያው የፌስቡክ 'ፖስት'-

አላስታውስም።

አወዘጋቢው 'ፖስት'-

ምናልባት ደመቀ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ያልኩበት? ወይም ደግሞ ስለ'ኤፍ-ዋን ቦንብ' የጻፍኩት?

ከፌስቡክ የተገለሉበት ረዥሙ ጊዜ-

ለወር እንኳ የቆየሁበት ጊዜ አላስታውስም።

ከፍተኛው ላይክ ያገኙበት-

ምን ሊሆን ይችላል? ህም…ምናልባት የሰኔ 16ቱን ሰልፍ ተከትሎ ብሮድካስት ባለሥልጣን የትግራይ ቲቪ ለምን አልዘገበም ያለ ጊዜ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በነዚህ ነጥቦች መልስ ሊሰጥ ይገባል ብዬ የጻፍኩት?

የላይኩ ብዛት፡-

አላስተውስም።

ለአንተ ተወዳጁ 'ፌስቡከር'፡-

ብዙ ጓደኛ ነው ያለኝ፤ እንዳታጣይኝ፤ ይለፈኝ ይሄ ጥያቄ። አንዳንዶቹ ከኔ የተሻለ የመጻፍ ችሎታ ያላቸው ግን ጊዜ የሌላቸው አሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሐሳብ ኖሯቸው ጽሑፍ ላይ ልምድ የሌላቸው አሉ። ጥሩ የሚጽፉ ሆነው ያልታወቁ፣ ቅርብ ጊዜ የጀመሩ ይኖራሉ። ሥነ ሥርዓት ያላቸው፣ ሐሳብ ያላቸው፣ ተራ ስድብ ውስጥ የማይገቡ፣ ለዛ ያለው ጽሑፍ የሚጽፉ አሉ። መጥቀስ ይቻላል፤ ግን ይቅርብኝ።

አስገራሚው ኮሜንት፦

ሰማያዊ ፓርቲ የመጀመርያ ሰልፍ የጠራ ጊዜ ሄጄ እዘግባለሁ ብዬ ነበር፤ ከሰልፉ በኋላ አንዱ ምን ብሎ ጻፈ - 'እኔኮ ላይህ ጓጉቼ ነበር። ጠብቄህም ነበረ። ለካስ ዳንኤል አንድ ሰው አይደለም' ብሎ የጻፈው አስቆኛል። ድርጅት ወይም ቡድን ናችሁ ማለቱ ነው።

ከማኅበራዊ ሚዲያ ምን አተረፍክ?

ሐሳቤን መግለጽ መቻሌ። ብዙ ሰው እንዳውቅ መሆኔ።

ከፌስቡክ ጡረታ የምትወጣበት ጊዜ

መውጣት አይቻልም። አስፈላጊም አይሆንም። ልቀንስ እችል ይሆናል።

በ70 ዓመትዎ 'ፖስት' የሚያደርጉት ምን ሊሆን ይችላል?

"የመሰለህን ተናግሮ ከመኖር በላይ ጸጋ የለም"

ዝቅተኛው ላይክ አግኝተህ የደነገጥክበት አጋጣሚ

የዛሬ 3-4 ዓመት አካባቢ የባህርዳር መስቀል አደባባይ ለሆነ ድርጅት ሊሰጥ ነው በሚል ሰልፍ ነበር። እኔ አጣርቼ 3 ሰዎች እንደሞቱ፣ በምን ሁኔታ እንደሞቱ ሁሉ ጽፌ ነበር። ሁሉም ሰው ግራ ስለተጋባ ነው መሰለኝ ዝም አለ። ምንም 'ሪአክሽን' አልነበረም እና ግራ አጋባኝ። መረጃው በራሱ የሚጮህ ስለነበረ ለምንድነው ሰው ዝም ያለው ብዬ ትንሽ ተደናገጥኩ? ተሳስቼ ይሆን ብዬ ሁሉ እንደገና ዜናውን ማጣረት ጀመርኩ። እሱ ትንሽ ሰርፕራይዝ አድርጎኛል።

ፖስት የምታይበት ፍጥነት፦

ያለምንም ላይክ መጻፍ ስለምችል ብዙም 'ቦዘር' አያደርገኝም።አንድ ፖስት ከለጠፍኩ በኋላ ብዙዉን ጊዜ ኮሜንቶቹን ተመልሼ የምመለከተው ከ24 ሰዓት በኋላ ነው። የተለየ ነገር ካልሆነ በቀር። ስንት ላይክ አለው? ስንት ኮሜንት አለው አላይም። ያ የሆነው ለምንድነው መሰለሽ…ስንጀምር ያን ጊዜ የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ ላይክም ላይኖር ይችላል። 4 ወይም 5 ላይክ ቢኖር ነው። ኢንተርኔቱም አስቸጋሪ ስለነበር ያኔ 'ላይክ' ውድ ነበር። ስለዚህ አሁን ብዙ ሰው ላይክ ባያደርግም መጻፍ ኖርማል ነው ለኛ።

አበረከትኩ የምትለው አስተዋጽኦ፦

የአገሪቱ ፖለቲካ ትርክት (ናሬቲቭ) ሚዛኑን እንዲጠብቅ፣ አንድ ወገን ብቻ ከበሮ እንዳይደልቅ፥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ነበረኝ ብዬ አስባለሁ። አሉታዊ አስተዋጽኦ የነበረኝ አይመስለኝም።

መረጃ ከየት ታገኛለህ?

ለእኔ መረጃ ማግኘት ከልምድ የመጣ ነገር ነው፤ በሚዲያ ላይ ረዥም ጊዜ ሰው ሲሠራ…ሚዲያ ላይ መሥራት ብቻ አይደለም፤ አንደኛ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ልጅ ሆኜ ጀምሮ አውቀዋለሁ። ረዥም ጊዜ ስከታተል፣ አዝማሚያዎችን ሳነብ፣ ግለሰቦቹ እነማን ናቸው…አውቀዋለሁ፤ አብዛኛው ፖለቲካ 'ሪሳይክል' ነው የሚሆነው፣ እኛ አገር። አዝማሚያዎቹ 'ትሬንዶቹ' ምን ይመስላሉ። ምን ሲሆን ምን ይከሰታል የሚለውን በጊዜ ርዝመት ማወቅ ችያለሁ። ሁለተኛ ደግሞ ከጊዜ ብዛት ብዙ 'ኮንታክት' ብዙ ግንኙነት አሉኝ። በሥራ አጋጣሚ የማውቃቸው፣ በተለያየ አጋጣሚ የማውቃቸው ብዙ ሰዎች በየቦታው ይኖራሉ። ስለዚህ በሂደት፣ በጊዜ ብዛት የመጣ 'ስኪል' ነው።

ተከፍሎህ ነው የምትጽፈው ስለሚባለው ነገር…?

ዌብሳይት ላይ እንኳ ስጽፍ ትንሽም ቢሆን የጉግል ማስታወቂያ ሊኖር ይችላል፤ ፌስቡክ ላይ ስለጻፍኩ ግን የተለየ የማገኘው ነገር የለም። ለሕዝቡን መረጃ መስጠት ካልሆነ።

ለምን ጠፋህ? መረጃ እያገኘህ አይደለም?

መረጃ አሁንም ሁልጊዜም አገኛለሁ፤ ግማሹ ስለማይመለከተኝ ነው የምተወው፣ ግማሹን ደግሞ አሁን ስካር የሚመስል ነገር በረድ እስኪል ድረስ ነው…መረጃ ሰጥቶ፣ መረጃ ወስዶ የማገናዘብ፣ ዳይጄስት ማድረግ፣ የሚያስችል ስክነት በሌለበት ሁኔታ [መጻፍ] ጊዜን ማባከን ነው፣ መረጃንም ማባከን ነው። ለዚህ ነው የቀነስኩት። ሰፋ ያለ ሥራም ለመሥራት እየተዘጋጀሁም ስለሆነ ነው። በዛ ላይ ሰበር ዜና የሚወድ አስተዳደር ስለመጣ እነሱ በሰበር ዜና ከተጠመዱ ለኔ ሥራ ይቀንስልኛል።

ዛቻዎች አሉ?

ሁልጊዜ የሚዝት አለ። ግማሹ ዛቻ ከፌስቡክ የማያልፍ ነው። ግማሹ ለወሬም የማይበቃ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉት በስም የምናውቃቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት 'አድሚን' ሆነው የሚመሯቸው የፌስቡክ ገጸች ናቸው ስድብና ዛቻ የሚጽፉት እንጂ ተራ ሰዎች አይደሉም። በክልል አመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ ገብተው ሲጨማለቁ እናያለን። ጥሩ ነገሩ ምንድነው አብረዋቸው የሚሠሩ ሌሎች ኃላፊዎች ደውለው ይሄ የግለሰብ ባሕሪ ነው፤የኛን ፓርቲ አይወክልም፤ ቀለል አድርገህ እየው ምናምን ይላሉ። ሁሉም አንድ ዓይነት አይደሉም።

ዛቻዎች ሲመጡ እኔ አመራሩ ውስጥ ብዙ ሰዎችን ስለማውቅ ይሄ ከናንት ነው ወይ እላለሁ። የማገኘው መልስ ሚዛኒን እንድጠብቅ ያደርገኛል። እንደኔ ያልሆነ ሌላ ሰው ግን፣ ያነሰ መረጃ ወይ ያነሰ ልምድ ወይ ያነሰ ኮንፊደንስ ያለው ሰው ግን [በነዚህ ዛቻዎች]እንዴት ሚዛኑን ሊያሳጣው፥ ሊያስረበግገው እና አገሩን ጥሎ ሊያስኬደው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከፍተኛ ወከባና ወጀብ ያለበት ነው ፌስቡክ።

የሚመሩበት የማኅበራዊ ሚዲያ መርሕ

አቋም መያዝ በራሱ ስሕተት አይደለም። ዋናው መርሔ ግን ጥሬ ሐቅን (fact) እና የግል አስተያየት (Opinion) አለመደባለቅ ነው።

'ደራሲ ያደረገኝ ማኅበራዊ ሚዲያው ነው'