የሊቢያው ትሪፖሊ አየር ማረፊያ የሮኬት ጥቃት ሙከራ ተደረገበት

የሊቢያ አየር ማረፊያ Image copyright AFP

በሊቢያ አገልግሎት የሚሰጠው ብቸኛው የአየር ማረፊያ በተደረገበት የሮኬት ጥቃት ምክንያት በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል።

በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ የሚገኘው ሚቲጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማክሰኞ ምሽት ገደማ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረበት።

በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ይኖር እንደሁ በውል እንዳልተላወቀ እየተነገረ ይገኛል።

ሊቢያ ውስጥ 27 ሰዎች በቦምብ ጥቃት ተገደሉ

በሊቢያ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎችን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ ተዘግቶ የቆየው ይህ አየር ማረፊያ ባለፈው አርብ ነበር እንደገና አገልግሎት መስጠት የጀመረው።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ኃይል መዲናዋ ትሪፖሊን ቢቆጣጠርም የተቀረው የሃገሪቱ ክፍል በታጣቂዎች ይዞታ ሥር ይገኛል።

የሮኬት ጥቃት እንደተሰነዘረ በታወቀ ጊዜ ከግብፅ ይመጣ የነበረ ንብረትነቱ የሊቢያ አየር መንገድ የሆነ አውሮፕላን ወደ ምሥራቁ የሃገሪቱ ክፍል አቅጣጫውን እንዲቀይር ተደርጓል።

ካለሁበት 1፡ ''በሜዲትራንያን ባህር ከመስመጥ መትረፌ ሁሌም ይደንቀኛል"

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተሰኘው ዜና ወኪል ምንጮቼ ነገሩኝ እንዳለው ሌሎችም በረራዎች ሚስራታ ወደ ተሰኘችው ከተማ አቅጣጫ ቀይረው በረራ እንዲያደርጉ ተገደዋል።

ሊቢያ አየር መንገድ ሃገሪቱ ውስጥ ብቸኛው አገልግሎት ሰጭ ሲሆን ወደተወሰኑ የዓለም ሃገራት በረራ ያከናውናል።

አየር መንገዱ፤ በደኅንነት ምክንያት ወደ አውሮጳ ሃገራት በረራ ማድረግ አይችልም።

ሊቢያ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣች