ሞትና መፈናቀል በአዲስ አበባ ዙሪያ

ተፈናቃዮች
አጭር የምስል መግለጫ ከተፈናቃዩቹ ህፃናትና አዛውንት ይገኙበታል

በሳምንቱ የመገባደጃ ቀናት በኦሮሚያ ክልል፥ ፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞን ባሉ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲጠፋ፥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደግሞ አካባቢዎቹን በመልቀቅ ወደአጎራባች የአዲስ አበባ ወረዳዎች ሸሽተዋል።

በጥቃቱ 23 ሰዎች ሲሞቱ በጥቃቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 200 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ናቸው በተባሉት አሸዋ ሜዳ፥ ከታ፥ ቡራዩ አካባቢዎች በተፈፀሙት ጥቃቶች የንብረት መውደም እና ዝርፊያ መፈፀሙንም የአገር ውስጥ የብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

በጥቃቶቹ ህይወታቸውን አጥተዋል የተባሉ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም ጥቂት እንዳልሆኑ ከአካባቢዎቹ ሸሽተው የወጡ ሰዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል::

ሁኔታው በተፈጠረበት ጊዜ ከሃገር ውጪ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፅህፈት ቤታቸው ኃላፊ በኩል ግድያዎቹን እና ጥቃቶቹን ያወገዙ ሲሆን፥ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጨምረው አስታውቀዋል።

. "ምንም ዓይነት ችግር እንዳይከሰተ ተዘጋጅተናል" ፖሊስ

ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከል ኡማም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መግለጫዎችን እሁድ ከሰዓት በኋላ ሰጥተዋል።

በጥቃቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብዙኃን መገናኛዎቹ በዘገባዎቻቸው አትተዋል።

በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፊሊጶስ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን የጎበኙት ምክትል ከንቲባው ጥቃቶቹ ቅዳሜ ዕለት በመስቀል አደባባይ ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች ከተደረገው ደማቅ አቀባበል ያልተገናኙ እንደነበሩ ተናግረዋል።

አጭር የምስል መግለጫ ጥቃቱ ተጣርቶ በተጠያቂዎች ላይ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል

ቢቢሲ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተገኝቶ በርካታ በጥቃቱ የተጎዱ ግለሰቦች የድንገተኛ ህክምና ክፍል ውስጥ እገዛ ሲደረግላቸው ተመልክቷል::

ሆስፒታሉ በውስጡ የሚታከሙ እና ወደሌሎች ሆስፒታሎች የተዛወሩ ተጎጅዎችን ዝርዝር መግቢያው ላይ የለጠፈ ሲሆን፥ ለተጎጅዎች እንክብካቤ በማድረግ ላይ የነበሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት የህክምና ባለሞያ ለቢቢሲ እንደገለፁት ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት ውስጥ "በድብደባ ምክንያት አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ይበዛሉ" ብለዋል::

ትናንትና እሁድ ከሰዓት በኋላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚሸሹ ተፈናቃዮች አስኮ ወደሚባለው የአዲስ አበባ አካባቢ በእግር ጉዞ ሲያቀኑ ቢቢሲ ተመልክቷል።

ጨቅላ ሕፃናትና የዕድሜ ባለፀጎች ከተፈናቃዩቹ መካከል ሲሆን ለመያዝ አመቺ የሆኑ እቃዎችን የተሸከሙ በርካታ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ ታይተዋል:: በመንገዳቸው ያገኟቸውን ተመልካቾች ውሃ ሲጠይቁም ነበር።

. ኦፌኮና ሰማያዊ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቁ

በቡራዩ ከተማ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ገደማ እንደኖረች ለቢቢሲ የገለፀች እና ከሁለት ልጇቿ ጋር የተፈናቀለች እናት ምሽቱን የት እንደምታሳልፍም ሆነ ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት እንደማታውቅ ተናግራለች። "ሁሉን ነገር ትቼ ነው የመጣሁት እንግዲህ።"

የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው በብዛት የሚገኙ ሲሆን ተፈናቃዮቹን ሲያጅቡ እና ሲያስተናብሩ ታይቷል።

ከቅዳሜ ምሽት አንስቶ በአስኮ ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስትያን ተጠልለው የቆዩ ተፈናቃዮች በአምስት አውቶብሶች በቅርብ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት ተወስደዋል።

አጭር የምስል መግለጫ በጥቃቱ የበርካቶች ህይወት ማለፉ ተገልጿል

በአካባቢዎቹ ቀደም ካሉት ቀናት አንስቶ ውጥረት የነበረ ሲሆን ከቅዳሜ አመሻሽ ጀምሮ ግን ሁኔታው ወደ አደገኛ ጥቃት መሸጋገሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል::

ምንም አይነት የፀጥታ አካላት ምላሽ ባለማግኘታቸው ጭንቅ ውስጥ የገቡት ነዋሪዎችም ለሚያውቋቸው ሰዎች በስልክና በማህበራዊ መገናኛ በኩል የድረሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር::

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ንጋት ላይ መኖሪያቸውን ትተው ነፍሳቸውን ለማትረፍ በአቅራቢያ ወደሚገኙ የእምነትና የመንግሥት ተቋማት የሸሹ ሲሆን ሌሎች ድግሞ በአዲስ አበባ ወደሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት በመሄድ የተፈፀመባቸው ጥቃት እንዲታወቅ አቤት ብለዋል::

. የኢትዮጵያ አየር ኃይል አልሸባብ ላይ ጥቃት ፈጸመ

ጥቃቱን በመሸሽ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተጠግተው ለሚገኙት ሰዎች የሚሆን ምግብና ውሃ ለማቅረብ ከከተማዋ መስተዳድር በተጨማሪ የተለያዩ ግለሰቦች ጥረት እያደረጉ ነበር::

በአካባቢዎቹ የፀጥታ ኃይሎች ቢሰማሩም ውጥረቱና ስጋቱ በአቅራቢ በሚገኙ ቦታዎች ላይም ይስተዋል ነበር::

በጥቃቱ ላጋጠመው የንፁሃን ሞት የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም እጃቸው አለበት የተባሉ ከ70 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ መግለፁ ተዘግቧል::