በአዲስ አበባ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ባጋጠመ ግጭት 5 ሰዎች ተገደሉ

ዘይኑ ጀማል

የፎቶው ባለመብት, FANA

በአሸዋ ሜዳ፣ ከታ እና ቡራዩ አካባቢዎች የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ በርካቶች ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አደባባይ በወጡበት ወቅት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ዛሬ ከሰዓት በሰጡት መግለጫ ''ብዛት ያለው የከተማዋ ነዋሪ አደባባይ ወጥቷል፤ በርካቶቹ ድምጻቸውን አሰምተው ተበትነዋል። የተወሰነው ኃይል ግን አዝማሚያቸው ሌላ ነበር፤ ህብረተሰቡን ለማሸበር እና ግጭቱን ለማስፋፋት ቦንብ ይዘው የወጡ ነበሩ'' ብለዋል።

ፒያሳ አካበቢም ዝርፊያ ለመፈጸም ጥረት ያደረጉ ነበሩ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ከጸጥታ አስከባሪዎችም መሳሪያ ለመንጠቅ ሙከራዎች ተደርገው ነበረም ብለዋል። ከአንድ የጸጥታ አስከባሪ ላይም መሳሪያ መነጠቁን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ተናግረዋል።

ከፖሊስ ጋር በተፈጠረው ግጭት የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና የቆሰሉም እንዳሉ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረው እንደተናገሩት የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ወጣቶችን በመመልመል እና ገንዘብ በመክፈል ያሰማራቸው ኃይል አለ ብለዋል።

ባለፉት አራት ቀናት በአዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ኮሚሽነሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ከቡራዩ እና አካባቢው የተዘረፉ ንብረቶችንም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጸመው ጥቃት በአንድ ማዕከል የሚመራ እና በሁለት ድርጅቶች ስም የሚንቀሳቀስ ቡደን ያቀነባበረው ተግባር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ''ወንጀሉን የፈጸሙት በሙሉ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው'' ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በአዲስ አበባ ወደ 300 የሚጠጉት፤ በቡራዩ ደግሞ ከ300-400 የሚሆኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ ''መንግሥት እና ፖሊስ በማንም ላይ ጉዳት እንዲደርስ አይሹም። ፖሊስ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ይህን ተልዕኮ ለመፈጸም ፖሊስ ማንኛውንም እርምጃ ይወስዳል'' ሲሉ አስጠንቀቀዋል።

''ሃገር ለማፍረስ እኩይ ተግባር የሚፈጽሙትን ለፍርድ ለማቅረብ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይጠበቃል። ወጣቶችም በእነዚህ እኩይ ተልዕኮ ባላቸው ቡድኖች ሊታለሉ አይገባም'' ሲሉ ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።