ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

ተፈናቃይ

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበት ቀን መቃረቡን ተከትሎ አመራሮቹን ለመቀበል በርካቶች ከተለያዩ የኦሮሚያ ሥፍራዎች ወደ አዲስ አበባ መትመም ጀምሩ።

ባለፈው ረቡዕ የኦነግ ደጋፊዎች በአንዳንድ አካባቢዎች የአዲስ አበባ አደባባዮችን እና የመንገድ ጠርዞችን በኦነግ ባንዲራ ማቅለም ጀመሩ።

ይህን ተግባራቸውን ከተቃወሙ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ግጭት ተከሰተ።

በግጭቱም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የቡራዩ ተፈናቃዮች በምስል

አቶ ዳውድ ኢብሳ ማናቸው?

ሐሙስ መስከረም 10 በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ውጥረት ሰፍኖ ዋለ።

በዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ለመቀበል በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመሩ።

በቡራዩ በኩል ወደ ከተማዋ ዘልቀው ለመግባት ጥረት ያደረጉ ወጣቶች ቡራዩ ከተማ ላይ በፖሊስ አማካኝነት ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ታገዱ።

የፖሊስን እርምጃ ተከትሎም በፖሊስ እና በወጣቶቹ መከከል ከፍተኛ ውጥረት ተከሰተ። በዕለቱ ሁለት ወጣቶች መሞታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ዓርብ መስከረም 11 የተከሰተውን ወንጀል የአዲስ አበባ ፖሊስ የያዘው ስለሆነ ዝርዝር የጉዳቱን መጠን አላውቀውም ብለዋል።

ከብዙ ፍጥጫ በኋላ በቡራዩ በኩል ወደ ከተማዋ ለመግባት ሙከራ ያደረጉት ወጣቶቸ ተፈቅዶላቸው ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ሆነ።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ የገቡት ወጣቶች አርብ ምሽትን በመስቀል አደባባይ አሳለፉ።

አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በመስቀል አደባባይ ለሚገኙ ወጣቶች ምግብ እና ውሃ በመውሰድ እራት ሲመግቧቸው የሚያሳዩ ምስሎች በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።

ሞትና መፈናቀል በአዲስ አበባ ዙሪያ

ከ2000 በላይ ሰልጣኝ ፖሊሶች የጤና እክል ገጥሟቸው ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ

ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ቡደን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ።

የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ በመስቀል አደባባይ ይጠብቋቸው ለነበሩ ደጋፊዎቻቸው ንግግር አደረጉ።

በመስቀል አደባባይ የነበረው ሥነ-ሥርዓት የለምንም የጸጥታ ችግር ተጠናቀቀ።

ፌደራል ፖሊስም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከ4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ መሳተፉን አስታወቀ።

መስከረም 12 ቅዳሜ ምሽት ብሔራ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው የተባሉ ጥቃቶች እና ዘርፊያዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ተፈጸሙ።

በጥቃቱ ከ23 ሰዎች በላይ መሞታቸው ተዘገበ። ጉዳት የደረሰባቸውም በርካቶች መሆናቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የሟቾች እና የተጎጂዎችን ቁጥር ከፍ ያደርጋሉ።

ጥቃት በመሸሽ በርካታ ዜጎች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የእምነት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

ሰኞ መስከረም 14 በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም በአዲስ አበባ ለተቃውሞ ሰልፍ በርካቶች አደባባይ ወጡ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በሰጡት መግለጫ ''በርካቶቹ ድምጻቸውን አሰምተው ተበትነዋል። የተወሰነው ኃይል ግን አዝማሚያቸው ሌላ ነበር፤ ህብረተሰቡን ለማሸበር እና ግጭቱን ለማስፋፋት ቦንብ ይዘው የወጡ ነበሩ'' ያሉ ሲሆን ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታወቀዋል።

የቡራዩ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ቅዳሜ ምሽት የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አአቶ ለማ መገርሳም በቡራዩና አካባቢዋ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል ብለዋል።

አቶ ለማ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለመቋቋም የክልሉ መንግስት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ይሰራል ብለዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ)፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ፣ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር፣ የኦሮሞ አንድነት ለነጻነት፣ የኦሮሞ አንድነት ግንባር እና ሰማያዊ ፓርቲ ሰሞኑን በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን አወግዘዋል። 7ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭቶች አሳሳቢና አሳዛኝ ናቸው ብለዋል።

ፓርቲዎቹ የመንሥስት ይህ አይነቱ ግጭት ከመከሰቱ በፊት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ እና ወንጀለኞችን በአስቸኳይ ከህግ ፊት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ በቡራዩና አካባቢው የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ቡድን ላሰማራ ነው ብሏል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጉዳቱ መንስዔ፣ ጉዳት እና ስፋት አጣርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንደሚያደርግ ኮሚሽነረር አዲሱ ገ/እግዚአብሄራ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከአሁን በኃላ የህግ ጥሰት እና የስርዓት አልበኝነት ባህሪ ያላቸው ድርጊቶችን መንግሥት አይታገስም ሱሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተጎጅዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ መቀጠል ባለበት ሁኔታ ላይ እራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን በፍጥነት ለመቅረፍና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።