ኦህዴድ አብዮታዊ ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ታሪክ ሊያደርጋቸው ይሆን?

ጠ/ሚ ዐብይ አህመድና የኦሮሚያ ርዕሰ-መስተዳደር ለማ መገርሳ

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በአዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና እንደሚመጣ ትናንት በጅማ ከተማ ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ሲጀምር አስታውቋል።

"የላቀ ሃሳብ ለተሻለ ድል" በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በድርጅቱ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የኦህዴድና የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ድርጅታቸው ለውጦችን በማድረግ አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዞ እንደሚመጣ ገልፀዋል።

ሊቀ-መንበሩ አዲሱ ፍልስፍና ምን እንደሆነ ፍንጭ ባይሰጡም ድርጅታቸው ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያንና ለተቀረው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚጠቅም አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዞ ይመጣል ብለዋል።

ኦህዴድ ከስሙና ከአርማው ባሻገር የድርጅቱን ፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለም እንዲሁም የኦሮሞ ህዝብ የሚያደርገውን ትግል ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያደርሱ አዳዲስና ወጣት አመራሮችን ይፋ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

ኦህዴድ ፍልስፍናዬን እቀይራለው ሲል ምን ማለቱ ይሆን? ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር ግርማ ጉተማ በጥቅሉ ሲመልሱ "ኢህአዴግን እንደ አዲስ መፍጠር ነው። ህወሃት ሲየጠቀምባቸው የነበሩትን እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ዲሞክራሲ ማዕከላዊነት ያሉ ነገሮችን አራግፎ ማስቀጠል ነው የሚመስለኝ "ይላሉ።

የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ የሚችለው በአካባቢው መነፅር ሲታይ ነው የሚል እምነት በፓርቲው የተያዝ የሚመስላቸው መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ለምሳሌ የኦሮሞ የኢትዮጵያን ብሄርተኝነትም ከአፍሪካኒዝም ጋር በማያያዝ ነው ችግሩ ሊፈታ የሚችለው። አካባቢው አንድ አይነት ህዝቦች ብዙ ቦታ የተከፋፈሉበት ከመሆኑ አንፃር ደግሞ የኦሮሚያን ችግር ለመፍታት ኦሮሚያ ላይ ብቻ መስራት ዋጋ እንደማይኖረው የተገነዘቡ ይመስላል።

ይልቁንም በአካባቢያዊ ደረጃ መስራትና ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ በማመን ድርጅቱ አቅጣጫውን ሊለውጥ ይችላል። በዚህም ይዞ የሚመጣው አዲስ ፍልስፍናም ይህን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ምልከታቸውን ያስቀምጣሉ።

በተመሳሳይ እርምጃውን በአዎንታዊነቱ የሚመለከቱት የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ለውጡ ፓርቲው የሰራቸውን ስህተቶች ማረሚያ መንገድ ነው ብለውም ያምናሉ።

"ሥርዓቱ የተናጋው በድሮው መንገድ በድሮው አካሄድ ሊቀጥል ስላልቻለ ነው። አሁን ከዚያ አይነት ቀኖናዊ እርምጃ ተላቀናል ማለት ነው" ይላሉ።

እርምጃው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለሁሉም መልስ አለው፣ ሃሳብ ከአንድ ግንባር ብቻ ይመነጫል የሚሉትና መሰል ሃሳቦች እየተፈተሹ እንደሆነ ፤ ከሌሎች ጋር ለመጣመር የፓርቲያቸውን መሰረትና ድጋፍ ለማስፋትም እድሎች እንዳሉ አመላካች እንደሆነም ዶ/ር ዳኛቸው ያምናሉ።

"ህወሃት ማእከል ነበረች ያ ግን አሁን ቀርቷል መኪናውን የሚዘውረው ህወሃት አይደለም። አራቱም ተስማምተው ቢሄዱ ጥሩ ነው" ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትናንት በጉባኤው መክፈቻ እንደተናገሩት የኦሮሞ ህዝብ እስካሁን ያደረጋቸው ትግሎች ሳይሳኩ የቆዩት በነበረ መከፋፈልና የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ሳይዳብር በመቆየቱ ነው በማለት፤ ለዚህ ደግሞ አንድነትን ማጠናከርና ከለቅሶ ወጥቶ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦናን በመጎናፀፍ ወደቀጣይ የትግልና የድል አቅጣጫ መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

"ኦሮሞ ሌሎችን የሚያቅፍ እንጂ በባህሉ ሰውን አይገድልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተከባብረን አንድነታችንን በመጠበቅ መኖር አለብን።"

ጨምረውም ድርጅታቸው በተለያዩ መስኮች ጠንካራ አቅም ያዳበረ በመሆኑ ህዝቡንና ድርጅቱን ለማጥቃት የሚፈልግ ጠላት ካለ ይህንን ተገንዝቦ ከድርጊቱ በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።

በንግግራቸው ላይ ለኦሮሞ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትና ምርጫ ሆነው ከተመረጡ ኦህዴድ ስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌለው ተናግረው፤ "ነገር ግን አሁን የተገኘውን ድል ወደኋላ ለመመለስ ከጠላት ጋር የምትወግኑ ከሆነ ግን ከእነርሱ ለይተን አናያችሁም" ሲሉ ተናግረዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦህዴድ ምክትል ሊቀ-መንበርና ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳም የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀው "ከመከፋፈል፣ ጣት ከመጠቋቆምና በጠላትነት ከመተያየት ይልቅ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት አለብን" ብለዋል።

ድርጅቱ በጉባኤው ታሪካዊ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ያለፉት ሦስት ዓመታት ጉዞውን እንደሚገመግም ተገልጿል።