ኢትዮ-ኤርትራ፡ "አሁን ያገኘነው ሰላም፡ ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው" - ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል

ሳሚ በአስመራ ካቴድራል Image copyright ሳሚ ተስፋሚካኤል
አጭር የምስል መግለጫ ሳሙኤል በአስመራ ካቴድራል

"የኢትዮ ኤርትራ የሠላሙን ወሬ እንደሰማሁ፤ እነዚያን ከ 21 ዓመታት በፊት የተለየኋቸውን ቤተሰቦቼን ለማየት ነበር የጓጓሁት" ይላል በመንፈሳዊ መዝሙሮቹ የሚታወቀው ሳሙኤል ተስፋሚካኤል።

ይሄ እውን ሆኖ ወደተወለድኩባት ምድር መመለሴን ሳስበው ደግሞ ተመስገን ነው የምለው።

ሳሙኤል መጀመርያ ወደ አስመራ ከበረሩት አውሮፕላኖች ጋር ነበር ከአትላንታ ወደ አዲስ አባባ፡ ከአዲስ አበባ ደግሞ ወደ አስመራ ያመራው።

"1989፡ የ 12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው ከአስመራ የወጣሁት። ትንሽ ቆይቶ ጦርነቱ ተከተለ። ከአባቴ ጋር አዲስ አበባ ቆይቼ፤ ወደ አትላንታ ጆርጂያ አመራሁ" ይላል ኢትዮጵያዊ-ኤርትራዊው ሳሙኤል።

የትናንትናዋ እለት- በኢትዮ ኤርትራ ግጭት ቤተሰባቸው ለተለያየ?

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

ኢትዮጵያና ኤርትራ የመጨረሻውን የሠላም ስምምነት ፈረሙ

ጦርነቱ፤ ቤተሰቦቹ ላይ ጥቁር ጥላውን አጥልቷል።

"ሶስቱንም እህት ወንድሞቼን ካየኋቸው ዓመታት አለፉ። የስድስት ዓመት ልጅ ሆኖ የማውቀው ታናሽ ወንድሜ የ 27 ዓመት አዋቂ ሆኖ አገኘሁት፤ የአራት ዓመት የነበረችው እህቴም አግብታ፣ ልጅ ወልዳ ጠበቀችኝ። ከዚያ በኋላ የተወለደችው የቤታችን ታናሽ ደግሞ፤ ኮሌጅ ጨርሳ፣ ሥራ ይዛ ነው ያገኘሁዋት። በዘመኔ ይሄ ስቃይ አብቅቶ ስላሳየኝ አምላኬን አመሰግነዋለሁ'' ይላል።

ሳሚ ተስፋሚካኤል የኢትዮጵያና የኤርትራ ዜግነት ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘ ነው።

Image copyright ሳሚ
አጭር የምስል መግለጫ ሳሚ ከእናቱ ጋር

አባቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ እስኪሄድ ድረስ መሐል አስመራ፡ ዕዳጋ ሓሙስ በሚባለው አካባቢ ነው ያደገው።

ወወክማ የሚባለውን የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ሁሌም ይናፍቀዋል። የሚወደውን አክሮባት እዚያው አስመራ ጥሎት እንደወጣ ያስታውሳል።

ለረጅም ግዜ የተዋትን አስመራ፤ ዳግም ሲያያት ምን እንደተሰማው ሲገልፅ "የኤርትራ የአየር ክልል ላይ እስክደርስና መሬቷን እስክረግጥ ድረስ አላመንኩም ነበር" ካለ በኋላ በጨቅላነቱ ያየውን የምፅዋ አሰቃቂ ትውስታ ይተርክ ገባ።

አልሞት ባይ ተጋዳይነትና ሳሚ

"አክስቴና አያቴ ምፅዋ ይኖሩ ስለነበር በዕረፍት ግዜዬ እነሱጋ እሄድ ነበር።"

ድንገት እነርሱ ጋር ሳለሁ ጦርነት ተጀመረ። ጦርነቱ፤ ምፅዋን ለመቆጣጠር የኤርትራ ታጋዮች የከፈቱት ነበር። የተኩስ ልውውጡ መጀመርያ ላይ ቀልድ ነበር የሚመስለው፤ እየቆየ ግን እየበረታ ሄደ።

የአውሮፕላን ድብደባውና የከባድ መሣርያዎች ተኩስ ተጨምሮበት ነፍሴ ተጨነቀች። ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የት ድረስ አብረው ይራመዳሉ?

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት 20ኛ ዓመት - መቋጫ ያላገኘ ፍጥጫ

ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች

"አክስቴና ባለቤቷ፡ ካጠላብን ሞት እንወጣ ዘንድ፤ ከነበርንበት የገበያ አካባቢ ወደ መሃል ምፅዋ ይዘውን ሄዱ።"

"ከፊታችን ብዙ ሰዎች አስፓልት ላይ ሞተው፤ እያለፍናቸው ነበር የምንሸሸው።"

"ከሁሉም የማልረሳው ግን፤ በደንብ የማቃቸው የአክስቴ ጎረቤት የሆኑ ሁለት እህትማማቾች ሲሞቱ በዓይኔ በበረቱ አየሁ።"

ሌላ ግዜ ደግሞ፤ አንድ ሰው በአውሮፕላን ድብደባ የሞተች ሚስቱን በድንጋጤ አዝሏት እየሄደ ሳለ፤ መሞቷን ያዩ ቄስ 'አውርዳት' ብለው፤ ዓይኗ ላይ ትንሽ አፈር አልብሰውባት ትተናት ሄደናል።"

Image copyright Sami

ሳሙኤል፤ በወቅቱ 'የአልሞት ባይ ተጋዳይነት' ሲባል የተገለፀውን ጦርነት፤ ይህን በመሰሉ መጥፎ ትዝታዎች ነው የሚያስታውሰው።

"እስካሁን በህይወት ያለሁት፤ ያኔ ስላልሞትኩ ነው" ይላል።

ከብዙ ትግል በኋላ፤ ከሞት አምልጠን መስከረም በምትባለው መርከብ ከምፅዋ ወደ አሰብ ስንሄድ፤ እናቴ ደግሞ አሰብ ነበረችና፤ ከልጄ ጋር እሞታለሁ ብላ እኔ ጋር ለመምጣት ወደ ምፅዋ በመርከብ ስትጓዝ የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎች መርከቧን አቃጠሏት። መርከቢቷ የኢትዮጵያ ወታደሮችን የጫነች ስለመሰላቸው ነው ነበር ያጠቋት። እናቴና ሌሎች ተሳፋሪዎች ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ባህሩ ዘለው ሲገቡ፤ ሲቪል መሆናቸውን ያዩ ታጋዮች ታደጓቸው።

አያቴ በነጋታው፤ እናቴ የነበረችባት መርከብ መቃጠሏን በሰማች ግዜ፤ እንዲህ ታለቅስ ጀመር።

ውሃው ነው ወይ የበላሽ?

እሳቱ ነው ወይ የበላሽ?

አሳው ነው ወይ የበላሽ?

"ትንሽ ቆይቶ፤ እናቴ ስልክ ደውላ በህይወት እንዳለች ነገረችን።"

ሳሙኤል ዳግም እናቱን ያገኘው ግን፤ ከነፃነት በኋላ እርሷ ታጋይ ሆና ነው።

"ይህ ሰላም የፀሎታችን መልስ ነው። መጪው ዘመናችን፤ ስደት፣ ረሃብ እና ጦርነት የሌለበት፤ ሰላም የሰፈነበት ይሆን ዘንድ ነው'' የሚለው ሳሙኤል፤ ምንም እንኳ ሁለት ባንዲራ ቢኖረንም፤ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ ባይ ነው።

"አሁን ያገኘነው ሰላም፡ ከሰው ሳይሆን ከአምላክ ነው።"