አዲስ አበባ ለኑሮ ምቹ ያልሆነችው ከተማ

አዲስ አበባ ከተማ

ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሰው ጎርፍ ወደ አዲስ አበባ ይፈሳል። ሁሉም ህልማቸውን ሰንቀው፣ ነጋቸውን አልመው፣ "አዲስ አበባ ቤቴ"ን እያንጎራጎሩ ወደ አዲስ አበባ ይተማሉ። አዲስ አበባ ግን ሞልታ ትፈስ ጀምራለች።

በቂ የመኖሪያ ስፍራ፣ የንፅህና ቤት፣ መናፈሻ ስፍራ እና ሌሎች መሰረተ ልማት የላትም ይላሉ ያነጋገርናቸ የኪነህንፃ ባለሙያዎች። ከተማዋ እንግዶቿን አትምጡብኝ እያለች መግፋት ከጀመረች መቆየቷን ጨምረው ያስረዳሉ።

የከተማ ሕይወት መምራት የሁሉም ሰው ምኞት ይመስላል። ከተማ ውስጥ መኖር የብዙ ዕድሎችን በር ይከፍት ይሆናል። ከተሜ መሆን ስልጡንነት ነው። ግን ከተሞቻችን ለመኖሪያ ምቹ ናቸውን ስንል ለሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የኪነ ሕንፃ መምህሩ አቶ ኑረዲን መሐመድ ጥያቄ አቅርበናል።

እጥረት የተረፋት ከተማ

እንደ አቶ ኑረዲን ዜጎች ከተሞች ለመኖሪያነት ምቹ ናቸው እንዲሉ ከገጠሪቱ የሀገራችን ሁኔታ የተሻለ ሕይወት መምራት መቻል አለባቸው ይላሉ።

ለአቶ ኑረዲን ከተሞች የስራ እድልን ጨምሮ ንፁህ አየር፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ውሃ፣ መብራትና ለመኖሪያ ብቁ የሆነ ቤትን አሟልተው ማቅረብ ይገባቸዋል።

አቶ ታደሰ ግርማይ የኪነ ህንፃና የከተማ ፕላን እንዲሁም የአርኪዎሎጂና የቅርፅ ጥበቃና እንክብካቤ ባለሙያ ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው። እንደ እርሳቸው አንድ ከተማ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከየት ተነስቶ የት ይደርሳል የሚለው መታወቅ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ልክ እንደዛሬዋ አዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ችግር ይገጥማል ይላሉ።

እንደ አቶ ታደሰ፤ ከተማ በእቅድ ታስቦበት ሲሰፋ መልካም የሆነውን ያህል ያለእቅድ በዘፈቀደ የሚደረግ ማስፋፊያ ችግር ውስጥ እንደሚጥል አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ከተሞች ያላቸውን የተፈጥሮ ኃብት በአግባቡ ላላቸው ህዝብ የማያዳርሱ ከሆነ የመሰረተ ልማት እጥረቶቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እንዲጨምር፣ ወንጀል እንዲስፋፋ፣ ቆሻሻ እና የአየር ብክለት እንደሚያበዛ የሚናገሩት አቶ ታደሰ በዚህም የተነሳ ውጤታማ ያልሆነ ማህበረሰብ ወደ መፍጠር ሊኬድ እንደሚችል ያስረዳሉ።

አዲስ አበባ ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ያሉባት ከተማ እንደሆነች ያነሱት አቶ ታደሰ የከተማዋ አቀማመጥ ለጥ ያለ ካለመሆኑ የተነሳ በርካታ ህገወጥ ግንባታዎች የሚገነቡባት፣ በግንባታ ላይ ያሉ ህጎችን በአግባቡ ለማስፈፀም ችግር የገጠማት ከተማ መሆኑን እናያለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ አረንጓዴ ስፍራዎች ቢኖሩም በአግባቡ አገልግሎት እየሰጡ ስላልሆነ እንደሌሉ ነው የሚቆጠሩት የሚሉት አቶ ታደሰ ክረምት ሲመጣ በውሃ የሚጥለቀለቁ መንገዶች፣ ህገ ወጥ ሰፈራዎች፣ የመሰረተ ልማት እጥረቶች በከተማዋ በሰፊው እንደሚታዩ ጨምረው ይናገራሉ።

የምስሉ መግለጫ,

አንዳንድ የከተማዋ ስፍራዎች ከሚገባው በላይ በፎቆች የተሞሉና ምንም አይነት የመናፈሻ ስፍራ በሌለበት በአንድ ላይ ታጭቀው መተንፈስን እንኳ አስቸጋሪ አድርገውታል።

ሕይወት ከነትንታጓ የከተመችባቸውን ስፍራዎች

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ህይወት የማያንቀላፋባቸው ስፍራዎች መፈጠራቸውን የጠቀሱት አቶ ታደሰ እነዚህ ስፍራዎች ግን መተንፈስ አይችሉም ይላሉ።

ቦሌ መድኃኒያዓለም ኤድና ሞልና ካዛንቺስ ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ጀርባን ያነሱት አቶ ታደሰ በጣም ከሚገባው በላይ በፎቆች የተሞሉና ምንም አይነት የመናፈሻ ስፍራ በሌለበት መኖሪያ ቤት፣ ንግድ ቤት፣ ቢሮዎች በአንድ ላይ ታጭቀው መተንፈስን አስቸጋሪ አድርገውታል ይላሉ።

እነዚህ ህንፃዎች ሲሰሩ አረንጓዴ ስፍራዎች ታሳቢ መሆን ነበረባቸው ያሉት አቶ ታደሰ ፈረንሳይ አካባቢ፣ እንጦጦ ሲወጣ ያለውን አየር ከፒያሳ እስከ ሜክሲኮ ካለ አየር ጋር በማነፃፃር መሐል ከተማው ለመተንፈስ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ኑረዲን በበኩላቸው አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ በወጣትነት ዘመኑ የአካል አንቅስቀሰሴ የሚያዘወትርበት፣ የሕይወትን ትሩፋቶች ቁጭ ብሎ የሚያጣጥምበት እንዲሁም ህዝባዊ በዓሎችን የሚያከብርበት ስፍራ ቢፈልግ ከወዴት ያገኛል ሲሉ ይጠይቃሉ።

ለአቶ ኑረዲን አዲስ አበባ አንድ አለኝ የምትለው እንዲህ ያለስፍራ መስቀል አደባባይን ብቻ እንደሆነ በማንሳት በወጣትነት ጊዜም ሆነ በጉልምስና አረፍ ብሎ ለመቆዘምም ሆነ ለመሳቅ አረንጓዴ ስፍራዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ያነሳሉ።

ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ከተሞች

የኢትዮጵያን ከተሞች ምቹነት ካነሳን ምናልባት አንድ ወይም ሁለት ከተሞችን ልንጠቅስ እንችላለን ይላሉ አቶ ኑረዲን።

እነዚህ ከተሞችም ሀዋሳ እና ባሕርዳር እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ኑረዲን የከተሞቹ እቅድ ሰዎች መስፈር ከመጀመራቸው በፊት በሚገባ ስለተሰራ በቂ አረንጓዴ ስፍራ፣ ፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሁም መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አሏቸው ይላሉ።

አዲስ አበባ ለመኖሪያ ምቹ ካልሆኑ የአለማችን ከተማ አንዷ ናት የሚሉት አቶ ኑረዲን አዲስ አበባ ካላት ይልቅ የሌላት ነገር እንደሚበዛ ተናግረዋል።

ለአቶ ታደሰ ከባህር ዳርና ከሀዋሳ በተጨማሪም ጅማ እና አክሱም የህዝብ ቁጥራቸውም አነስተኛ መሆኑ ለመኖሪያ ምቹ ከሆኑ መካከል ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ከቁመት ያላለፉ ሕጎች

አዲስ አበባን መልከ ጥፉ ካደረጓት መካከል የሚገነቡት ህንፃዎች መሆናቸውን አንዳንዶች ይናገራሉ። ተመሳሳይ፣ በመስታወት የተለበጡ ህንፃዎች ከሽሮሜዳ እስከ ቃሊቲ ከአያት እስከ አስኮ ሞልተዋል።

ለአቶ ታደሰ አዲስ አበባ ያሏት ከህንፃ ጋር የተገናኙ ህጎች ከቁመት ያልዘለሉ መሆናቸው ለዚህ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ያምናሉ።

"አዲስ አበባ በአንድ አካባቢ ምን ያህል ቁመት ያለውና በስፋትም ቢሆን ምን ያህል ድረስ መገንባት እንደምንችል ይነግረን ይሆናል እንጂ እንደ ሌሎች ሀገሮች የግንባታውን ቁሳቁስ አይነት የሚወስኑ ተዛማጅ ህጎች የሉንም" ይላሉ።

እነዚህ ባለመኖራቸው እና ግንባታውን የሚያከናውነው ባለሙያው አቅም ውሱን መሆን የአዲስ አበባን የህንፃ መልከ ጥፉ እንዳደረገው ይናገራሉ።

በአንድ ስፍራ ከ4 ፎቅ እስከ 10 ፎቅ ድረስ መገንባት ይቻላል የሚል ህግ መኖሩ አቅም ያለው 10 የሌለው ደግሞ 4 ድረስ መገንባቱ ለአይንም ለመንፈስም አዋኪ የሆኑ ህንፃዎች እንድናይ እንዳደረገን ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ይላሉ አቶ ታደሰ ማስተር ፕላኑ ላይ ለአረንጓዴ ቦታ የታሰበው ስፍራ በሆነ አጋጣሚ ህንፃ ተሰርቶበት የሚታይበት አጋጣሚ አንዳንዴ ያጋጥማል ብለዋል።

ይህ ደግሞ ማስተር ፕላኑ ላይ ያለውን በአግባቡ የማስፈፀም ክፍተት መኖሩን ወይም ለማስፈፀም ብቃትና ጥራት እንደሚያንስ ያሳያል ይላሉ።

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ግን በህንፃ ግንባታው ዘርፍ ሙያዊ ስነምግባር አለመኖሩ በርካታ ችግሮች እንደፈጠረ የሚያነሱት አቶ ታደሰ "የሙያ ስነምግባር ከሌለ ህጎች በራሳቸው አያስኬዱም" ሲሉ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።