የአለም የምግብ ቀን: አስገራሚ የአለማችን ምግቦች

ምግብ Image copyright Getty Images

የምንበላው ምግብ የባህላችንና የማንነታችን መገለጫ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። በባህሎች መካከል ያለ ልዩነት ደግሞ ስለምግቦች ያለንን መጥፎም ይሁን ጥሩ አመለካከት ይወስነዋል።

ምንም እንኳን አንድ ምግብ ስናይ እንዳንወደው የሚያደረገን ሰውነታችን እራሱን ከበሽታ ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ቢሆንም፤ ሁሉም ሰው በስምምነት የሚጠላው ምግብ አለመኖሩ ደግሞ የባህልን ተጽዕኖ ያሳያል።

ስለ አንጀታችን የማያውቋቸው ስድስት አስገራሚ እውነታዎች

የአስር ደቂቃ እንቅስቃሴ የማስታወስ ችሎታን እንዴት ይጨምራል?

ዛሬ ጥቅምት 6 2011 የዓለም የምግብ ቀን ነው። ከዚህ ጋር አያይዘን በአለም ላይ ስላሉ የተለያዩ አስገራሚ ምግቦች ያገኘነውን መረጃ ልናካፍላችሁ ወደድን።

እስቲ የትኞቹን ምግቦች ይወዷቸው ይሆን?

በትል የተሞላ የገበታ አይብ (ጣልያን)

Image copyright Anja Barte Telin

በትልቅ ሰሃን ላይ አይብ ይደረግና ዝንቦች መጥተው እንቁላላቸውን እንዲጥሉበት መሃሉ ክፍት ይደረጋል።

የዝንቦቹ እንቁላሎች ተፈጥሯዊ ሂደታቸውን ተከትለው አይቡ ውስጥ መፈልፈል ይጀምራሉ። በዚህ ሰአት አይቡ መሰባበርና መቅለጥ ይጀምራል። ይህ ደግሞ ለአይቡ የተለየ ጣእም ይሰጠዋል።

የዚህ ምግብ ተመጋቢዎች ገበታ ላይ ሲቀርቡ የሚፈነጣጠሩት ትሎች ወደ አይኖቻቸው እንዳይገቡ መጠበቅ ያለባቸው ሲሆን፤ በህይወት ያሉትን ትሎች እንዳይበሉም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

ለጤና ከሚኖረው ጠንቅ በመነሳት አውሮፓ ውስጥ ምግቡ እንዳይሸጥ ተከልክሏል።

የበሬ መራቢያ አካል (ቻይና)

Image copyright Anja Barte Telin

የበሬ መራቢያ አካል የሚበላው ለጤና ካለው ከፍተኛ ጥቅም ሲሆን፤ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለስንፈተ ወሲብ ፍቱን መድሃኒት ነው ይላሉ።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ሴቶች ነጭ የሆነውን አካል መብላት ያለባቸው ሲሆን፤ ወንዶች ደግሞ ጠቆር ያለውን የበሬ መራቢያ አካል መብላት ይጠበቅባቸዋል።

የተጠበሰ አንበጣ (ዩጋንዳ)

Image copyright Getty Images

በየምግብ ቤት ከምናገኘው የተጠበሰ ድንች በተቃራኒው ዩጋንዳና አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ አንድ ሁለት ቢራ ከጠጡ በኋላ የተጠበሱ አንበጣዎችን ቃም ቃም ማድረግ የተለመደ ነው።

በዚህ ሀገር ሴቶች ይህንን ምግብ የማይበሉ ሲሆን፤ ተሳስተው ከበሉት ደግሞ ልክ እንደ አንበጣዎች አይነት ጭንቅላት ያለው ልጅ ይወልዳሉ ተብሎ ይታመናል።

የጉንዳን እንቁላል (ሜክሲኮ)

Image copyright Getty Images

እንደ አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች የአሁኗ ሜክሲኮ ተብላ በምትጠራው ሀገር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከዛፍ ላእ የሚያገኟቸውን የጉንዳን እንቁላሉች እንደ ቆሎ ይበሏቸው እንደነበር ይገልጻሉ።

በአካባቢው ሰዎች ' ኢስካሞልስ' ተብሎ የሚጠራው ምግብ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ከጉንዳኖች እንቁላል ጋር በመጥበስ ይበላል።

የእባብ ልብ (ቪየትናም)

Image copyright Getty Images

አሁንም ይህ ምግብ በቪየትናም ለስንፈተ ወሲብ ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ይታሰባል።

በመጀመሪያ እባቡ ይገደልና በውሃ ይቀቀላል። በመቀጠል የሰውነት ክፍሎቹ በባለሙያዎች ይበለትና ልቡ ለብቻው ይወጣል። ልቡን ለማወራረድ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች አብሮት እባበ ደም ይቀርባል።

የእባቡ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ቢሆን ለምግብነት ይውላሉ።

የበግ አይንና አንጎል (ኢራን፣ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ)

Image copyright Mo Styles

እንደ አጋጣሚ በእነዚህ ሀገራት የመሄድ አጋጣሚ አግኝተው ቢሰክሩና ጠዋት ላይ ህምም (ሃንጎቨር) ቢሰማዎት በአቅራቢያዎት ያሉ ሰዎች መጀመሪያ የሚያቀርቡልዎት ምግብ 'ካሌ ፓሽ' ይባላል።

የሚሰራውም ከበግ አይን፣ አንጎል፣ እግርና አንጀት ነው። ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ደግሞ የቀመሱት መስክረውለታል።

የተቀቀለ የአሳማ ደም (እንግሊዝ )

Image copyright Getty Images

'ብላክ ፐዲንግ' ተብሎ የሚጠራው የእግሊዞች ባህላዊ ቁርስ ተቀቅሎ የተጠበሰ የአሳማ ደም ከጎን ይጨመርበታል።

ለሰውነታችን ጠቃሚ የሆኑትን አይረን፣ ዚንክ እና ፕሮቲን በውስጡ እንደሚገኙም ይነገርለታል።

የእንቁራሪት ጁስ (ፔሩ)

Image copyright Getty Images

'ቲቲካካ' ተብለው የሚጠሩት በመጥፋት ላይ የሚገኙት የእንቁራሪት ዝርያዎች ፔሩ ውስጥ ከእንቁላል፣ ማር እና ቅመማቅመሞች ጋር ተፈጭተው እንደ ጁስ ይጠጣሉ።

እንቁራሪቶች የተቀላቀሉበት ጁስም ሃይል ሰጪ ከመሆኑ በተጨማሪ እዚህም ጋር ለስንፈተ ወሲብ ጠቃሚ እንደሆነ ይታሰባል።

የአይጥ ወይን (ቻይና)

Image copyright Mo Styles

ይህንን ተወዳጅ ወይን ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ይፈጃል። በመጀመሪያ ሩዝ ከሞቱ የአይጥ ልጆች ጋር ይቀላቀላል። አይጦቹ ጸጉር እንዳእኖራቸው ስለሚፈለግ ገና በቀናት እድሜ ያስቆጠሩ አይጦች ለዚህ ወይን ይመረጣሉ።

በቻይናውያን ዘንድ የአይጦች ወይን ለመድሃኒትነት ሲያገለግል፤ የወገብ ህመምን፣ አስም እና የጉበት በሽታዎችን እንደሚፈውስ ይታመናል።

የአሳ መራቢያ ፈሳሽ (ሩሲያ)

Image copyright Getty Images

'ሞሎካ' የምግቡ ስም ሲሆን፤ ዋና ግብአቱ አሳዎች ለመራቢያ የሚጠቀሙት ፈሳሽ ነው። ሩሲያ ውስጥ በየዕለቱ የሚበላና ተቀዳጅ ምግብ ነው።