"የመከላከያ ሚኒስቴርን በተሻለ መልኩ መምራት ይቻላል" ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የመጀመሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሾማለች።

በዚህ ታሪካዊ ቀንም የቀድሞዋ የኮንስትራክሽን ሚንስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ መሾም በጭራሽ ያልጠበቁትና ለመናገርም ቃላት እንደሚያጥራቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በተለይም የመከላከያ ሚኒስትርን ጨምሮ ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት ቦታዎች ሴቶች ተሹመውም ሆነ ተወክለው ስለማያውቁም፤ በዚህ ቦታ ላይ መሾምን እንዲህ ይገልፁታል።

"ለኢትዮጵያ ሴቶች ክብር ነው፣ እኔ ለተወለድኩበት አካባቢ ክብር ነው፣ ለግሌም ክብር ነው።የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ትልቅ ግዙፍና ታሪካዊ ኃይል ከመምራት በላይ ክብር የለም ብየ ነው የወሰድኩት" ይላሉ።

ወደ መከላከያ ከመምጣታቸው በፊት ወደ ሚዲያው አይን የገቡት የኮንስትራክሽን ሚኒስትርነት በነበሩበት ወቅት ላይ ሲሆን፤ በሚኒስትርነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት በአፋር ብሔር ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የአደጋ መከላከል ቢሮ አመራር ነበሩ።

በአፋር ክልል የተለያዪ የስልጣን ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፤ በ2008 ዓ.ም በተደረገው የመንግሥት ምደባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ሶስት ሴቶች ሆነው የተመደቡ ሲሆን የነበረውንም ሁኔታ እንዲህ ያስታውሱታል።

" ሶስታችንም የኢትዮጵያ ሴቶች ምሳሌ ሆነን መስራት አለብን በሚል መንፈስ ነበር የምንሰራው፤ ስህተት እንኳን ብንሰራ ያ ስህተት የመጣው ባለመቻሏ ነው ከሚል ጋር ነው የሚያያዘው። ሴት ስንሆን ስህተት መስራት ካለመቻል ጋር ነው በቀጥታ የሚያያዘው" ይላሉ።

በቀጣዩ ዓመትም በ2009 በተደረገው የሚኒስትሮች ሹመት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር በመሆን ለሁለት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ ግዙፍ ኢንዱስትሪና የሀገሪቱን ትልቅ በጀት የሚይዝ ከመሆኑ አንፃር ኃላፊነቱም ቀላል እንዳልነበር ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለች ሀገር ናት። ያስፈልጋሉ የሚባሉ ነገሮችን ለማደራጀትም ሆነ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮችን የማስተካከል ስራዎችንም እየሰራሁ ነበር" ብለዋል

የሁለት ሴት ልጆችና የአንድ ወልድ ልጅ እናት የሆኑት ኢንጂነር አይሻ ተወልደው ያደግኩት ሰሜን አፋር አካባቢ በምትገኝ ትንሽ መንደር ሲሆን አባታቸው በመንግሥት ሰራተኝነት አሰብ ወደብ ተቀጥረው ይሰሩ ስለነበር ወደ አሰብ የመጡት በልጅነታቸው ነው "ነፍስ ያወቅኩት አሰብ እያለሁ" ነው ይላሉ።

አባታቸው ወደ ዋናው ቢሮ አዲስ አበባ ሲዛወሩ እሳቸውም አብረው መጡ፤ ሁለተኛ ደረጃንም አዲስ አበባ ነው የተማሩት። ከልጅነታቸው ጀምሮ መሐንዲስ መሆን ይፈልጉ የነበሩ ሲሆን ህልማቸውንም አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲን ተቀላቅለው በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ በመመረቅ አሳክተዋል።

"ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ የተማርኩት አዲስ አበባ ስለሆነ፤ በምህንድስና ሙያም ተቀጥሬ በተለያዩ ቦታዎች ስለሰራሁ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ ማለት ይቻላል" በማለት በሳቅ መልሰዋል።

ወደ ፖለቲካ ህይወታቸው ከመግባታቸው በፊት በምህንድስና ሙያ የተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉት ኢንጂነር አይሻ ስራን ሀ ብለው የጀመሩት የቀድሞው ጂአይዜድ (ጂቲዜድ) ውስጥ ነው፤ በመቀጠልም ሰመራ ዪኒቨርስቲ ሲገነባ ሳይት ማኔጀርም ነበሩ።

ወደ ፖለቲካው እንዴት ገቡ?

ከመሐንዲስነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዴት ተቀላቀሉ ለሚለው ጥያቄ ኢንጂር አይሻ ሲመልሱ በመጀመሪያ የአፋርን ህዝብ ጥያቄን በቅርበት ለማየት ወደ አፋር በሔዱበት ወቅት እንደተጠነሰሰ ይናገራሉ።

"አፋር ስለሆንኩኝ አካባቢ ያለውንም የህዝቡን ሁኔታንም ሆነ ኑሮን ለማገዝ ክልሉ በሰጠኝ ዕድል መሰረት ወደ አፋር ተመለስኩኝ" ይላሉ

በአፋር ውስጥ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆንና የሴቶች የስራ መደራረብ ጫና ከፍተኛ መሆን ብዙ ያሳስባቸው የነበረ ሲሆን በተደራጀ ሁኔታ ለመታገል የተወሰነ ጊዜ ጥናት እንዳደረጉም ይናገራሉ።

መሰረታዊና መዋቅራዊ የሆኑ የሴቶችስ ጥያቄ በፖለቲካዊ መንገድ እንዴት ይመለሳል? የአፋር ሴቶችን ትግል ወደፊት ለመግፋት፣ ማስተካከያም ለማምጣት የኢህአዴግ አንዱ አጋር ፓርቲ የሆነውን የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ። ማዕከላዊ ኮሚቴም አባል የተቀላቀሉት ወዲያውኑ ነበር።

"ህዝቡን ማገልገል እንዳለብኝ ነው የሚሰማኝ ምክንያቱም ህዝብ ሲኖር ነው እኛም የምንኖረው የሚል እምነት አለኝ። ህዝብ ለመኖር ደግሞ የሚያስፈልገውን ነገር ማግኘት አለበት፤ በተለይ ሴቶች ደግሞ ያለብን ድርብርብ ጭቆናዎች በተወሰነ መልኩ መቀረፍ ስላለበት ያንን ለማድረግ ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን ስችል ብቻ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው የፖለቲካ ፓርቲውን የተቀላቀልኩት" ብለዋል።

ለባለፉት አስርት ዓመታት የብሔር፣ የመደብና ሌሎች ጥያቄዎች እንደ ፖለቲካ ጥያቄዎች ከመነሳት አልፎ የተለያዩ ምላሾችንም ለመስጠት ተሞክራል።

ምንም እንኳን ሴቶች በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ቢሆኑም ጥያቄያቸው እንደ ፖለቲካ ጥያቄ አለመታየቱ፣ ሴቶች ኮታን ከሟማላት ውጭ በመንግሥት የስልጣን መዋቅር ውስጥ አለመካተታቸውና እንዲሁም በስልጣን ቦታ ላይም ከተቀመጡ ለሴቶች ተብለው የተያዙ ቦታዎች ላይ ይቀመጡ ነበር።

ሰሞኑን በነበረው የካቢኔዎች ሹመት ላይ የነበረው አሰራር ተቀይሮ አምሳ ፐርሰንቱ ለሴቶች ከመሰጠት በተጨማሪ የመንግሥት ቁልፍ ቦታዎችንም አግኝተዋል። ይህንን በተመለከተ ኢንጅነር አይሻ የሚሉት አላቸው።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ባህል ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግና፣ የሚነገሩትም ተረት ምሳሌዎች ብዙዎች ሴቶች ልጆች ላይ ሰርፆ ስለሚያድጉ "አንችልም" የሚለውን ስነልቦና ይዘው እንደሚያድጉ ይናገራሉ።

"እኛ ራሳችንም አንችልም የሚል ስነ ልቦና ስላለን፤ እነሱም አይችሉም የሚለውን ይዘው ይመስለኛል እነዚህ ቁልፍ ቦታዎች የማይሰጡት" ይላሉ

ነገር ግን ማንኛውም ቦታ ላይ የሚሰራ ስራ አለ ብለው የሚያምኑት ኢንጅነር አይሻ " ያደግንበትን አይችሉም ወይም እኛም አንችልም የሚለውን ባህል ያለመተው አለ። ዋናውም ችግሩ እሱ ነው" ይላሉ።

በዓመታት ውስጥ መንግሥት ሴቶችን "ለማብቃት" በሚለው ፕሮግራም ለሴቶች ልዩ ድጋፍ (አፈርማቲቭ አክሽን) እንደ እቅድ አስቀምጦ የሰራ ሲሆን ሴቶችን በፖለቲካው፣ በትምህርቱ፣ በኢኮኖሚው ራሳቸውን እንዲችሉ ቢሰራም ውጤታማነቱ ላይ ጥያቄ አላቸው። በርካታዎቹም ስራዎችም ውጤታማ እንዳልነበር ይናገራሉ።

ይህ ሴቶችን በሆነ አካል ድጋፍ ማብቃትና ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ በሚኒስትርነት ደረጃ መሾማቸው ለየት ያለ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጅነር አይሻ " እኛ እንደምንችል ማሳየት አለብን ብየ ነው የማምነው" ይላሉ።

አምሳ ፐርሰንት የካቢኔው ሹመት ሴቶች የተሾሙበትን ምክንያት ሴቶች ከሙስና የፀዱ በመሆናቸውና ስራቸውንም አክብረው ይሰራሉ በሚል ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያን የፈጠረ ሲሆን በዚህ ላይ ኢንጅነር አይሻ የሚሉት አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስራ ሂደቶች የሚያገኟቸው ሴቶች ባህርይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚናገሩት ኢንጅነር አይሻ "ሴቶች በባህርያቸው ትርፍ ፈላጊ ናቸው ብየ አላምንም፤ ነገር ግን የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው መጠን ሁሉም ሴቶች መልአክ ነው ብየ አልወስድም። ሴቶች ባየኋቸው ቦታዎች ላይ ተጠንቅቆ የመስራት፣ በሌብነትም ምሳሌ ሲሆኑ አይታይም። ይህ ማለት ሌቦች የሉም ማለት አይደለም። ኃላፊነት ሲሰጣቸው የቻሉትን ያህል ማድረግ እንጂ በጥፋት ሲወገዙ አልሰማሁም፤" በማለት ኢንጅነር አይሻ ይናገራሉ

ለዓመታት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳ መሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳ ከመቆየቱ አንፃር፤ ሹመቱም ሆነ ውክልናው እንደ መልካም ጅማሮ ብዙዎች ቢያዩትም መስረታዊና መዋቅራዊ የሚባሉ የሴቶችን ችግር ሊቀርፍ ይችላል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ።

የኢትዮጵያን ሴቶች ችግር መቶ በመቶ ይቀረፋል ብለው ኢንጂነር አይሻም የማያምኑ ሲሆን "የሴቶች ችግር በኛ ብቻ የሚቀረፍ እንዳልሆነ አውቃለሁ። አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ ግን ግን ሊቀርፈው ይችላል ብየ አስባለሁ " ይላሉ።

ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሚኒስትሮች መሆን ለወደፊቱ ለሚመጡት ህፃናት ሴቶች አርዓያ እንደሚሆኑና የሴቶችንም ጥያቄ የመግፋት ጅማሮ ከመሆኑ አንፃር እንደ ቀላል መታየት እንደሌለበት ይናገራሉ።

ሴቶች በባህርያቸው የማስተዳደር ስጦታ አላቸው ብለው የሚያምኑት ኢንጅነር አይሻ መንግሥታት ሴቶችን ወደ አስተዳደርና ወደፊት ቦታ ሊያመጡ እንደሚገባም ይመክራሉ።

የመከላከያ ሚኒስትሩን እንዴት ሊመሩት አስበዋል

ለሴቶች ሊሰጡ አይገቡም የሚባሉ ቦታዎች ሊኖሩ እንደማይገባ የሚያምኑት ኢንጅነር አይሻ የመከላከያ ሚኒስትርነት ከባድ እንደሆነ ቢታሰብም ያላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

"ይህንን ግዙፍ፣ ታሪካዊና በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ዕውቅና ያለው ተቋም መምራት ቢቻል የተሻለ አድርጎ ለመምራት፣ ያንን ማድረግ ቢያንሰኝ ግን ካለበት ዝቅ እንዳይል ተቋሙን ለመምራት መዘጋጀት አለብኝ ብየ ነው የማስበው" ይላሉ።

በዋነኝነትም የአገሪቷን ዳር ድንበር ማስጠበቅ፣ የአገሪቷን ፀጥታና ሰላም ማስከበርና የዜጎችን ልማትን ማገዝ ዋና አፅንኦት የሚሰጠው ስራ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን " የህዝብን ጥያቄን ለመመለስ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መምራት አለበት ብየ አምናለሁ። ከዚያም በተጨማሪ አገሪቷ ያለችበትን የጂኦ ፖለቲካል ሁኔታንም በብልህነት ካለው አመራር ጋር መምራት ያቅታል ብየ አላምንም፤ ሲሆን በተሻለ መልኩ መምራት እችላለሁ" ይላሉ።

ምንም እንኳን ያለውን የመከላከያ አሰራር ማስቀጠል ዋና አላማቸው ቢሆንም አሁን ሀገሪቷ እየሄደችበት ካለው ለውጥ ጋር ለማጣጣም የተወሰነ ማሻሻያ እንደሚኖር አልደበቁም።

በተለያዩ ቦታዎች በሀገሪቷ ግጭት በተለይም በብሔር ግጭት እየተናጠች ከመሆኗ አንፃር ያንን እንደ አንድ ፈተና ቢያዩትም ያንን በኃላፊነት የሚያይ የሰላም ሚኒስትር የተቋቋመ ሲሆን ከዛ የተረፈው ወደ መከላከያ ሚኒስትር እንደሚመጣም ተናግረዋል።

"በዋናነት የሀገራችንን ውስጣዊ ሰላም ማስጠበቅ አለብን። የምታሰባስበን፣ የማንነታችን መገለጫ ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርገን ማቆየት የምንችለው ሰላማዊ ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት በአገራችን ሲኖር ነው። ነገር ግን በርካታ ልናስባቸው የሚገቡ ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ብየ አምናለሁ። በተቻለ መጠን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታትና በሰላም አሁን እንደጀመርነው ከጎረቤቶቻችን ጋር መኖር መቻል አለብን። " ይላሉ