የአብን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ አዲሱ ካቢኔ አማራን ያገለለ ነው ይላሉ

የአብን ሊቀምነበር የሆኑት ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ

የፎቶው ባለመብት, FB/Dessalegn Chanie Dagnew

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አዲሱን ካቢኔያቸውን አዋቅረዋል፤ የተመጣጠነ የብሔርም ሆነ የፆታ ተዋጽዖ እንዲኖረው ብዙ መለፋቱንም ሐሙስ ዕለት በነበረው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጉባዔ ፊት ቀርበው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀሩት ኢዲሱ ካቢኔ ካልተዋጠላቸው ግለሰቦች መካከል በቅርቡ የተመሠረተው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔ ናቸው። ሊቀ መንበሩ አሁን ስላለው የፖለቲካ 'ጨዋታ ሕግም' የሚሉት አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀሩት ካቢኔ የተስማማዎት አይመስልም. . .

ዶ/ር ደሣለኝ፦ በጥንካሬ ደረጃ ከዚህ በፊት ከነበረው ባልተለመደ መልኩ ከሴቶች ሹመት አንጻር የተሻለ ነው። ብሔርን እና የብሔራዊ ፓርቲዎች ተዋጽኦ ላይ ግን ችግር እንዳለበት ታዝቢያለው።

ምን ጎደለ?

በግልጽ እንዳየነው ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሾሙት ሰዎች የፖለቲካ ካፒታል የሌላቸው እና የፓርቲውም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልሆኑ ጭምር ናቸው። እነኚህ ሰዎች የአማራን ሕዝብ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ማስከበር የሚችሉ መሆናቸው እርግጠኛ የማይኮንባቸው ግለሰቦች ናቸው። ከዚህ ቀደምም የማይታወቁ እና የፖለቲካ ዕውቅና የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እኔም እንደ አንድ የአማራ ብሔርተኛ ድርጅት መሪ፤ ዐብይ አሕመድ አማራውን ከወሳኝ የፌደራል መንግሥት የሥልጣን ቦታዎች እንዲገለል እያደረገ እንደሆነ ነው የምረዳው።

ሁለተኛ ድክመቱ ወሳኝ የሚባሉ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የውጭ ጉዳይ ውስጥ አንድም አማራ አለመካተቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገዳዳሪያቸውን ስልታዊ በሆነ መልኩ እያገለሉ እንደሆነ ያሳያል።

አምባገነን መንግሥታት የሚያደርጉት የሥልጣን ማደላደል እና ሥልጣን ጠቅልሎ የመያዝ እርምጃ ነው እያየሁ ያለሁት።

ከላይ የሴቶች ተዋጽኦን አድንቀው አልፈዋል። በዚህ ውስጥ የጾታ ተዋጽኦን ነው የሚያዩት ወይስ ምን ያህል አማራ አለ የሚለውን ነው የሚመለከቱት? ማለ ቅድሚያ የታየዎት ጾታቸው ነው ወይስ ብሔራቸው?

ኢህዴግ የተመሠረተው በብሔራዊ ፓርቲዎች ጥምረት ነው። ከነዚህም መካከል አንዱ አዴፓ ነው። አዴፓን በፌደራል መንግሥት ወክለው ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚሰየሙ ሰዎች የአማራን ሕዝብ ወርድ እና ቁመቱን የሚመጥኑ መሆን አለባቸው። ሴቶች የሚገባቸውን የካቢኔ ቁጥር ማግኘታቸው ትክክል ቢሆንም።

እርሶ የጠቅላይ ሚንስትሩን ካቢኔ እንዲያዋቅሩ ዕድሉ ቢሰጥዎ ምን ያህል የአማራ ተወላጅ ሚኒስትር አድርገው ይሾማሉ?

በቅድሚያ እኔ ያነሳሁት ጥያቄ ቁጥሩ በዛ ወይም አነሰ የሚል አይደለም። ከ20 ካቢኔ አባላት 4 ወይም 5 አማራዎች አሉ። ይህም ብዙ የሚያስከፋ አይደለም። ያነሳሁት ጥያቄ ሆነ ተብሎ ጠንካራ የአዴፓ ተወካዮች ቦታ አልተሰጣቸውም ነው። ለምሳሌ በአዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው የተመረጡት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ናቸው። ዶ/ር አምባቸውን እዚህ ካቢኔ ውስጥ አለማካተት ማለት ተሰሚነት ያላቸውን አዴፓዎች ሆነ ተብሎ ገሸሽ የማድረግ ስልት ነው።

እርስዎ በጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ ውስጥ የአማራ ውክልና እንዲጎላ የሚፈልጉትን ያክል በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁሉም ብሔሮች ውክልና እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ? 80 የሚኒስትር ቦታ የለም። ይህን የሁሉንም ፍላጎት እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

ሁሉንም ብሔር ለመወከል 80 የሚኒስትር ቦታዎችን መፍጠር አትችልም። ብቃት እና የሕዝብ አገልጋይነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕዝብ ቁጥር ብዛት መሠረት ቦታዎች መሰጠት አለባቸው።

በዚህ ስሌት ከሄድን፤ ኦሮሞ በርካታ ቁጥር አለው። ስለዚህ በርካታዎቹ ከኦሮሞ መሆን አለባቸው ብለው ያምናሉ ማለት ነው?

ለምን እንደዛ ይሆናል?

ውክልናው በሕዝብ ብዛት መሆን አለበት ስላሉኝ።ኢህአዴግ የተዋቀረው ከአራት ብሔራዊ ፓርቲዎች ስለሆነ፤ ከእነዚህ ፓርቲዎች የተሻለ አቅም እና ዕውቀት ያለው ሰው ነው ሊወጣ የሚችለው። አሁንም ቢሆን [በእርስዎ ስሌት ከሄድን] አንድ አፋር ወይም ሶማሌ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚስትር የመሆን ዕድል ላይኖረው ነው. . . ?

አሁን ባለን የፖለቲካ አደረጃጀት መሠረት ከአፋር ወይም ከሶማሌ ወደ ከፍተኛ ሥልጣን ሊመጣ የሚችልበት ዕድል የጠበበ ነው።

ስለዚህ በእርስዎ ስሌት አንድ የአፋር ሕጻን ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ማለም የለበትም?

እየተከተልን ባለነው የጎሳ ፌደራሊዝም ሥርዓት ውስጥ የብሔር ቁጥርን መሠረት ያደረገ አሠራር ነው ያለው። ያ ማለት ግን የሌሎች ብሔር ተወካዮችም ወደ ሥልጣን መምጣት የለባቸውም ማለት አይደለም። ብሔርን ብቻ መሠረት ያደረገ ሹመት ተገደን የገባንበት ሥርዓት ሆኖ እንጂ ብቃትን መሠረት ያደረግ ሥርዓት የአማራ ሕዝብ የረዥም ጊዜ ፍላጎት ነበር።

አሁን ደግሞ ተገደን የገባንበት ሥርዓት ነው ወደሚል ሐሳብ እየመጡ ነው። ቀደም ብዬ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ ስዋቀሩት ካቢኔ ስጠይቀዎ የአማራ ውክልና በተገቢው ሁኔታ የተሟላ እንዳልሆነ ሲያስረዱኝ ነበር።

ቁጥሩ አነሰ አላልኩም።

መቼም በጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት አማራ ብቻ ቢሆኑ ቅር ይልዎታል አይደል?

አዎ ቅር ይለኛል። አሁን ያለው ፖለቲካ በዜግነት ላይ የተመሠረት ፖለቲካ አይደለም። ሕገ-መንግሥቱ የሚለው እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እንጂ የኢትዮጵያ ዜጎች አይልም። በብሔር ተደራጅቶ ፍላጎትን ማስጠበቅ በሚቻልበት ሥርዓት ውስጥ አማራውም በብሔሩ ተደራጅቶ ጥቅሙን እና ፍላጎቱን መጠየቅ አለበት።

አሁን ከሰጡኝ አስተየየት በመነሳት እርስዎ ወደፊት አሁን ከሚያራምዱት የብሔራዊ ፖለቲካ ወጥተው የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱበት ዕድል እንዳለ ይሰማኛል።

እወጣለሁ ብዬ አላስብም (ከብሔር ፖለቲካ)። ምክንያቴን ላስረዳ። የዜግነት ፖለቲካ ወደ መድረኩ ቢመጣ እንኳ በአማራው ላይ ከዚህ ቀደም የደረሰበት ግፍ እና መከራ ተመልሶ እንዳይመጣበት በብሔሩ ተደራጅቶ እራሱን መጠበቅ እንዳለበት አስባለሁ። አማራ ሁሌም አማራዊ አደረጃጀቱን ይዞ መቀጠል አለበት።

በፌስቡክ ገጽዎ ላይ ካሰፈሩት ጽሑፍ ውስጥ «የፌደራል ወሳኝ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኦሮሞ መውረርና መቆጣጠር ለአማራው ሕዝብ ዓይን ያወጣ ክህደት እና ሸፍጥ ነው» ይላል። ቀደም ብሎ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትሩ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች የአማራን ሕዝብ ፍላጎት ያስጠብቃሉ ብለው እንደማያምኑ እንጂ ከቁጥር ጋር የተገናኘ ቅሬታ እንደሌሎት ነው የነገሩኝ። ሐሳቡ የሚጋጭ ይመስላል።

የኦሮሞ ውክልና በዝቷል ማለት ሳይሆን፤ ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የሰጧቸው ሹመቶች በኦሮሞዎች የማሲያዝ እና አማራን የመግፍት አዝማሚያዎች አሉት የሚል ነው። ለዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት አማራ ከፍተኛ ድጋፍ እና አስተዋጽኦ አድርጓል። ወደ ሥልጣን ከመጣም በኋላ የመጀመሪያውን ድጋፍ ያገኘው ከአማራ ሕዝብ ነው። አሁን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በአማራ ሕዝብ ላይ በግልጽ እየፈጸመ ካለው ክህደት መቆጠብ አለበት። እያወራ ያለው ሌላ ነው፣ የሚሠራው ሌላ ነው።

ሰው መሾም ያለበት በብቃቱ መሆን አለበት እያሉ የምናየው ነገር ግን ብቃት ያላቸውን አማራ እያገለሉ ከእሳቸው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች የመውረር ሁኔታ እየታዘብን ነው። ህወሓት ፈጽሞታል እያልን ስንቃወም የነበረውን ጉዳይ አሁን በኦሮሞው ሲደገም የማንቃወምበት ምክንያት የለም።

ከብሔር በተጨማሪ ደግሞ የሃይማኖት ውክልና ጥያቄም አለ። አሁን ያለው የሚኒስትሮች ብዛት 19 ነው። መቼም ለብሔር እና ሃይማኖት ውክልና ተብሎ 80 እና ከዚያ በላይ ሚንስትር መሥሪያ ቤቶች አይመሰረቱም። ከዚህ ዓይነሁኔታ በቀላሉ መውጣት ይቻላል?

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዚህ ዓይነት ችግር እንላቀቃለን ብዬ አላስብም። ለዚያም ነው የእኛም ፓርቲ በተጻፈ የጨዋታ ሕግ የአማራን ሕዝብ መብት እና ፍላጎት ማስከበር አለብን የምንለው። የጨዋታው ሕግ የሚቀየር ከሆነ ደግሞ ወደፊት የምንመለከተው ጉዳይ ይሆናል።

ታዲያ እንደሱ ከሆነ የጨዋታውን ሕግ ለመቀየር መታገሉ አይሻልም?

እሱን እኮ ሞክረነዋል። የአማራ ሕዝብ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምን የፖለቲካ ፓርቲ በመመሥረቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ይህም ውጤት አላመጣም። አማራው ብቻውን ይህን ለመቀየር የሚታገልበት እና ሌላው በራሱ ጊዜ በብሔሩ የሚደራጅበት ጥቅሙን እና ፍላጎቱን የሚያስከብርበት እና ከዚያም አልፎ አማራውን የሚያጠቃበት ሥርዓት በመፈጠሩ እኮ ነው አማራ ተገፍቶ ወደዚህ የገባው።

የጠቅላይ ሚንስትሩን የካቢኔ ሹመት በመቃወም የአዴፓ ተሿሚዎች ከካቢኔ ጥለው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። አዴፓ ይህን የሚያደርገው ይመስልዎታል?

አዴፓ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ ትልቁን የአማራ ሕዝብ ወክሎ ነው እዚያ የሚገኘው። ትልቅ ጉልበት አለው። የማስገደድ አቅም አለው። ይህንን ማድረግ የማይችል ከሆነ ደግሞ ሕዝባችን ከዚህ ቀደም አምባገነን መንግሥቶችን ከትከሻው አንስቶ ሲፈጠፍጥ አንደነበረ ሁሉ ዛሬም ታግሎ ራሱን ነጻ ያወጣል። ሕዝባችን ጥቅም እና መብቱን ማስከበሩን ይቀጥላል። የዐብይ አሕመድ መንግሥት ያዋቀረው ካቢኔ የአማራን ሕዝብ የሚመጥን አይደለም። ተስፋ አለኝ አዴፓም ይህን የካቢኔ ሹመት የሚመለከት መግለጫ ያወጣል የሚል፤ እምነት አለኝ።

ይህን አቋም በፓርቲ ደረጃ ትወስዳላችሁ?

ይህ ትልቅ የፖለቲካ ክስተት ስለሆነ የአብን ሥራ አስፈጻሚ ሁኔታውን ይገመግማል ብዬ አስባለሁ። ምን አቋም እንደሚወስድ ግን ከስብሰባው በኋላ የሚታወቅ ነው የሚሆነው። እስካሁን የገለጽኩልህም የግል ምልከታዬን ነው።