መዝገቡ ተሰማ፡ ተፈጥሮን በብሩሹ የሚመዘግበው ሠዓሊ

ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

ተማሪ እያለ ጠረጴዛ ላይ ሥዕል በመሳሉ በተማሪዎች ፊት ተገርፏል፤ የሒሳብና የአማርኛ ደብተሮቹን ራስጌና ግርጌ በሥዕሎቹ በማሳበዱ ኩርኩም ቀምሷል።

የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን፤ ካርታ፣ የሰው አካል ክፍሎች፣ ሌሎች በሥዕልና በሞዴል የሚገለፁ አጋዥ ቁሳቁሶችን በመሥራትና ማስታወቂያዎችን በድርብ ጽሑፍ በመጻፍ ለትምህርት ቤቱ ውለታ ውሏል።

እርሱ ራሱ ለምን እንደሆነ ባያውቀውም ድሮ ድሮ እግር ኳስ የሚጫወት ልጅና ደብተር የያዙ ልጆችን መሣል ያዘወትር ነበር።

አድናቂዎችን ማፍራት የጀመረውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ታዲያ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ስሙ ገኗል፤ ስንቶቹን አስደምሟል፤ ስንቶቹን በማመንና ባለማመን አሟግቷል!

መዝገቡ በሥራዎቹ ትንግርት ነው። ተፈጥሮን ይገልጣል፣ ስሜትን ያንጸባርቃል፣ ሥነ ልቦናን ያሳብቃል፣ ቀለሞቹን በብርሹ አጥቅሶ ሸራዎቹ ላይ ያፋቅራል። ሥራዎቹን ያዩት ሁሉ "ኦ! መዝገቡ!" የሚሉት ወደው አይደለም።

ሥዕሎቹ በካሜራ እንጂ በሠዓሊው ጣቶች የተገለጹ አይመስሉም።

እርሱ ግን ማነው ካሜራን ከሥዕል ያላቀው? ይላል።

"በሥልጣኔ ታሪክ ፎቶግራፍ የመጣው ከሥዕል በኋላ ነው፤ሥዕልን ፎቶግራፍ ይመስላል ማለት ማሳነስ ነው" ሲል የሥነ ሥዕልን ታላቅነት ይሞግታል።

"በተለይ የእኛ ማኅበረሰብ ከሥዕል ይልቅ ፎቶግራፍን ነው የሚያውቀው" የሚለው ሠዓሊው "አድናቆትን ለመግለጽ፤ 'እውነተኛ ይመስላል' የምንለውም ለዚሁ ይመስለኛል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

ይህንን ሲል የፎቶግራፍን ጥበብ አንኳሶ አይደለም ታዲያ።

አንዳንዴ በሥዕል ለመግለጽ የተፈለገን አካል ወይም ቦታ ሙሉ ለሙሉ ማስታወስ ሊቸግር ስለሚችል በጣም ጥልቅና ዝርዝር ነገሮችን ለመሥራት የግድ ፎቶግራፍ አሊያም ሞዴል መጠቀም ሊያስፈልግ እንደሚችል ያስገነዝባል።

የቀለም አወቃቀር፣ ብርሃንና ጥላ ከልምድ የሚመጣ በመሆኑ አይቸገርበትም፤ ነገር ግን ውህደት (Composition) ማዋቀሩ የምንጊዜም ተግዳሮት በመሆኑ ዘወትር መጠበብን ይጠይቀዋል።

የገሃዱን ዓለም የማስመሰሉን ጥበብ ከተሻገረው ግን ዓመታት ተቆጥረዋል።

ዕል አቡጊዳ

ገና በልጅነት ዕድሜው አድናቆትንም ግሳጼንም በማስተናገድ ያለፈው መዝገቡ፤ የሥዕል ሥራን 'ሀ...ሁ' ያለው በትምህርት ቤት እንደሆነ ይናገራል።

ያኔ ድሮ ከመምህራንና ከተማሪዎችም አድናቆት ይጎርፍለትም ነበር፤ ደብተርህን ለምን ታቆሽሻለህ ከሚል ኩርኩም በላይ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ብትገባ የሚሉት ቁጥራቸው ይበረክት ነበር።

በወቅቱ የሚያበላና የማያበላ ሥራ ብሎ የሚያስብ ጭንቅላት አልነበረውም፤ ወላጆቹም ይህንን ከቁብ አልቆጠሩትም፤ አንድም ቀን ሳት ብሏቸው 'ይሄ የምትሞነጫጭረውን ምናምንቴ ተው!' ሲሉ አልገሰጹትም።

ያደገው ገጠር አካባቢ በመሆኑ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ስለመኖሩ ከነ አካቴው አያውቅም ነበር። ሥዕል ሰዎች ባላቸው ተሰጥዖና በልምድ የሚሠሩት እንጂ በትምህርት ያገኙታል ብሎ ስለማሰቡም እንጃ።

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

"አንድ ሰው ልምምድ አድርጎ በትምህርት ሲደገፍ ዐይን የሚይዝ ጥሩ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፤ አድናቆትን የሚያስቸር፣ በሰዎች ስብዕና ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል፣ ሚዛን የሚደፋ ነገር መሆን አለበት" ይላል።

እንዲህ ዓይነት ሥራዎችንም መሥራት የጀመረው የሁለተኛ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ እንደሆነ ይናገራል።

የመጀመሪያዬ የሚለው ሥራውም "ቤተሰብ" ይሰኛል፤ ሦስት ክፍሎችም አሉት፤ ካደገበት ማኅበረሰብና ቤተሰብ ተቀድቶ የተሣለ ነው።

"ገጠር ውስጥ ቤተሰብ የሚለው ሐሳብ በራሱ ሰፊ ነው፤ የቤት እንስሳት ሁሉ እንደ ቤተሰብ አባል ይቆጠራሉ፤ የእገሌ ልጅ እንደሚባለው፤ የእገሌ ፍየል፣ የእገሌ በሬ ይባላል" የሚለው ሠዓሊው ይህንን ለማጉላት ሥዕሉን እንደሠራው ያስረዳል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ወንድ ሴቶችን የመጠበቅ፣ የቤተሰቡንና የራሱን ክብር የማስጠበቅ እሴት ይሰጠዋል። ይህንንም የሚያጎላ ሐሳብ ተካቶበታል - በበኩር ሥራው።

ተፈጥሮን የሚመዘግበው መዝገቡ

መዝገቡ እውናዊ (Naturalistic/ Realistic/ Expressionist) የሥዕል አሳሳል ዘዴን ከሚከተሉት ሰዓሊያን በጉልህ ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያ የሥዕል ታሪክ የትኛው የአሳሳል ዘዴ ተቆናጦ እንደቆየ ለመናገር ቢያስቸግርም ለምሳሌ በደርግ ዘመን የእውናዊ የአሳሳል ዘዴን እንደ አንድ የፕሮፖጋንዳ ጥበብ ለዐሥራ ሰባት ዓመታት ይጠቀሙበት ነበር።

በሠዓሊና ሃያሲ ስዩም ወልዴ ግለ ታሪክ መጽሐፍ (ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ) በደርግ ጊዜ የሌሎች አገራት መሪዎችን ለመቀበል የመሪዎቹን ምሥል በትልቅ ሸራ ላይ ይሥሉ እንደነበር ተጠቅሷል። ይህንንም ለንግግሩ ዋቢ ማድረግ ይቻላል።

እርሱ ግን ገበያውንና ጊዜውን አይቶ ሳይሆን የልጅነት ህልሙ እንደሚመራው ይናገራል።

ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ያለው የመንገዱ ጠመዝማዛነት፣ የምንጮቹ፣ የዳገቱ፣ የመስኩ፣ የዕጽዋቱ፣ የከብቶቹ…በልጅነት አዕምሮው መዝገብ ሰፍረዋል፤ ይህም አሁን ለሚከተለው እውናዊ የሥዕል አሳሳል ዘዴ መነሻ እንደሆነው ይገልጻል።

በወቅቱ አካባቢውን እንዲያይ፣ እንዲያደንቅ፣ እንዲመረምር፣ የፈለገበት ቦታ እንዲሄድም ቤተሰቦቹ ይፈቅዱለት ነበር። ይህም ከመልክዓ ምድሩ ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮለታል።

ከዚህም ባሻገር የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ እውናዊ ሥራዎች እንዲሠሩ የሚጠይቅ ነበር፤ እርሱን አሟልቶ ያልሠራ ተማሪ መቀጠል አይችልም ነበር፤ ስለሆነም የትምህርት ሥርዓቱ ብርታት ሆኖታል።

የሥዕል ሥራዎቹ ረቂቅ ስሜቶችና ሥነ ልቦና ይንጸባረቁበታል። "ይህ ግን በአንድ ጊዜ ተሳክቶ የሚመጣ አይደለም" የሚለው መዝገቡ ሁል ጊዜ በዝርዝር የሚገለፁ ነገሮችን ከመሣል በፊት "ጥናትና ሙከራ አደርጋለሁ፤ የሰው ባህሪ ከነ መልኩ መዋሃዱን በተደጋጋሚ አጤናለሁ፤ ውጤታማ እስከሚሆን መሥራትንም እመርጣለሁ" ብሏል።

አውታረ መጠን (3D)

ይህን አሳሳል ዘዴ ሠዓሊና ሃያሲ ስዩም ወልዴ አውታረ መጠን ይሉታል።

በጥንት ግሪክ ሠዓሊዎች ይተገበር ነበር፤ ከዚያም በህዳሴው ዘመን እንደ ዋና የአሳሳል ዘዴ ይጠቀሙበት ነበር፤ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ተቀባይነት ከማጣቱም አልፎ ሠዓሊዎች ሥዕል ሁለት አውታረ መጠን ነው፤ በመሆኑም ጠፍጣፋ ሆኖ መቀመጥ አለበት በሚል ሃሳብ እንደሚሟገቱ ያብራራል።

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

ሦስት አውታረ መጠን የሚያስመስል( Illusion) እንዳይኖር ጥረት ያደርጋሉ፤ ነገር ግን ቀለማቱ ብቻ የሚፈጥሩትን የቀለም ክፍተት ማስወገድ አይቻልም ይላል።

የሸራ ቅርፅ በራሱ የመስኮትነት ባህሪ አለው። መስኮት ደግሞ የሚያሳየው ከሸራው ቀጥሎ እንጂ ከሸራው ወዲህ አይደለም ሲል ግልጽ ምሳሌ ያጣቅሳል።

"የገሃዱ ዓለምም ሦስት አውታረ መጠን እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተፈጠረው፤ ቋሚ፣ አግዳሚና ጥልቀት ናቸው። ይህንንም ወደ ሸራ ወስዶ ለማምጣት በሚፈለግበት ጊዜ የጥቁረትና ንጣት ግንኙነት፣ የሞቃትና የቀዝቃዛ ቀለማት ውህደት፣ የመቅላትና ሰማያዊ በማድረግ ወደ እውነታው ዓለም የተጠጋ እንዲሆን አድርጎ መሳል ይቻላል" ሲል ያብራራል።

በመሆኑም ይህንን ጥበብ ለማስወገድ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ማጉላቱ ወደ እውነታው ያስጠጋል በሚል ለዚህ የአሳሳል ዘዴ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ጀመረ።

በጊዜ የነገሰው 'ንግ'

የንግሥ በዓል በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው፤ ሰዎች አዳዲስ ልብስ ለብሰው፤ አጊጠው ፤ እየጨፈሩ፤ እየዘመሩ ያከብሩታል።

ይህ የልጅነት የንግሥ በዓል ትውስታው በሸራው ላይ ያሰፍረው ዘንድ ወትውቶታል።

የንግሥ በዓልን ቁልጭ አድርጎ የሚሳየው ሥዕል 10 ስኩየር ሜትር ሸራ ላይ ያረፈ ሲሆን በሥዕሉ ላይ በርካታ ሰዎች ያሉበትና የየራሳቸው የፊት ቅርጽ፣ አለባበስ፣ የስሜት አገላለጽ በዝርዝርና በጥልቀት የተሠራ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

የጥናት ጊዜውን ሳይጨምር ቀለሙን ብቻ ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታትን ወስዷል።

የሥዕል ሥራዎቹ ለዕይታ በቀረቡበት አውደ ርዕይ የይደገም ጥያቄን ያስተናገዱ ናቸው፤ በአገር ውስጥ በሚገኙ ቅንጡ ሆቴሎችም ሥራዎቹ ይገኛሉ።

"እንደ ንግሥ ዓይነት ትላልቅ ሥራዎችን ሽጬም ሆነ ለመሸጥ አስቤ አላውቅም፤ በዋጋ ተምኛቸው ባላውቅም እንደየ ጊዜውና አንደ ዋጋ ግሽበቱ ተለዋዋጭ መሆኑ አይቀርም" ይላል ሠዓሊ መዝገቡ።

ለዚህም በአገር ውስጥ ለጥበብ የሚሰጠው ትኩረትና ለተመልካቾች ቅርብ የሚደረግበት ልምድ እምብዛም አለመሆኑን ያነሳል።

"በሌሎች አገራት የሥዕል ሥራዎችን ማሳያ ቦታ አለ፤ ለመሸጥም አስማሚዎች አሉ፤ ዋጋም የሚተመነው በእነርሱ አማካኝነት ነው፤ አገር ውስጥ ግን ጠንካራ የሥዕል ማሳያ 'ጋለሪ' እንኳ የለም፤ ስለዚህ ዋጋው ይሄን ያህል ነው ማለት አልችልም" ሲል ምክንያቶቹን ያስረዳል።

ሥዕሎችም እንደ ሰው ዕድል አላቸው ብሎ የሚያምነው መዝገቡ እንደ ልጆቹ የሚሳሳላቸው ሥራዎቹ ከእርሱ ጋር መቆየታቸው ይመርጣል።

ከዚህ ቀደም ባሳያቸው ሁለት የሥዕል አውደ ርዕዮች ሥራዎቹ በሰዎች ላይ የፈጠረው ስሜት እንዳሳሳውና ማበረታቻ እንደሆነውም ይናገራል።

አሁን በሚያስተምርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የርሱን ፈለግ የተከተሉ ተማሪዎችን ማፍራት ችሏል፤ በጎ ተፅዕኖም እንዳደረገ ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Mezgebu Tesema

የመዝገቡ 'ሙድ'

በተለይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ደራሲዎች፣ ሠዓሊዎች ፣ ሙዚቀኞች፤ ሥራዎቻቸውን የሚሠሩበትና ፍላጎት የሚፈጥሩ መልካም አውድ 'ሙድ' ይፈልጋሉ።

ገጣሚ፣ ደራሲና የመብት ተሟጋች ማያ አንጀሎ ምንም እንኳን ቤት ቢኖራት ለመጻፍ የሆቴል ክፍል ትከራይ ነበር።

ጆርጅ ኦርዌል አልጋ ላይ ወይም ሶፋ ላይ በጀርባው ጋደም ማለትን ሲመርጥ በተቃራኒው ቻርለስ ዲከንስ ቆሞ መጻፍ ይመቸዋል።

ቪክቶር ሁጎ ልብሱን አወላልቆ እርቃኑን ካልሆነ የሥነ ጽሑፍ አድባር አትጠራውም።

ፈረንሳዊው የልቦለድ ጸሐፊ ባልዛክ በቀን 50 ስኒ ቡና ካልጠጣ የጥበብ አውሊያዎች ዝር አይሉለትም ነበር። መዝገቡስ?

"የራሴ ስንፍና፣ የመሥራት ፍላጎት፣ ጥንካሬና ጉድለት ካልሆነ በስተቀር ምንም የሚረብሸኝ ነገር የለም" ይላል።

ሥዕሎቹን ለመሥራት የትም መሄድ፣ ምንም ማድረግ አይጠበቅበትም።

ከቤተሰቦቹ ጋር ተመካክሮ ፈቃድ በማግኘቱ የሥዕል ስቱዲዮውን የመኖሪያ ቤቱ ሳሎን ውስጥ አድርጓል።

ልጆች ቢቦርቁ፣ ዘመድ አዝማድ ቢያወራ፣ ቡና አጣጭ ቢያሽካካ ከጀመረው ሥራ አንዳችም የሚያናጥበው ምድራዊ ኃይል የለም።