ሁለት መንታ እህትማማቾች ከሰርጋቸው ጥቂት ቀናት በፊት መታገታቸውን የተመለከቱና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የታገቱት እህትማማቾች

የፎቶው ባለመብት, Bala Dauran Family

ኢትዮጵያ

• የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኑዮ ጉቴሬዝ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላለፉ።

ለመላው ኢትዮጵያውያንም የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት በመምረጣችሁ እና አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲይዙ ስላደረጋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ዩጋንዳ

• አንዲት ዩጋንዳዊ የሬድዮ ፕሮግራም አቅራቢ እንደገቢ ማሰባሰቢያ የሚያገለግል ትዳር ከስራ ባልደረባዋ ጋር ልትፈጽም ነው።

ሉሉ ጄሚማህ የተባለችን ጸሃፊ ወደ እንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለመላክ በሚውለው ሰርግ ታዳሚያን ገንዘብ ከፍለው መግባት አለባቸው።

ናይጄሪያ

• በሰሜን ምስራቃዊ ናይጄሪያ የሚገኙ ሁለት መንታ እህትማማቾች ከሰርጋቸው ጥቂት ቀናት በፊት ታገቱ።

ለዘመዶቻቸው የሰርግ ልብሳቸውን ለማሳየት በሄዱበት ነው ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር ባልታወቁ ሰዎች ታፍነው የተወሰዱት።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ

• በዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚገኙ ሰባት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድነት የሚወክላቸውን አንድ እጩ በመጪው ወር እንደሚመርጡ አስታወቁ።

በደቡብ አፍሪካ የተሰባሰቡት ፓርቲዎቹ ተስማምተው አንድ እጩ ያቀርባሉ የሚለው ዜና ብዙዎችን አስገርሟል።

ሳኡዲ አረቢያ

• ቱርክ ውስጥ የተገደለው ጋዜጠኛ ጃማል ካሾጊ የመጀመሪያ ልጅ ሳላህ ካሾጊ ሳኡዲ አረቢያን ለቅቆ ከነቤተሰቡ አሜሪካ ገባ።

ከዚህ ቀደም በአባቱ የተነሳ ከሃገር እንዳይወጣ እገዳ ተጥሎበት ነበር።

ህንድ

• በደቡባዊ ህንድ የኬራላ ግዛት ፖሊስ ከአመጽ ጋር በተያያዘ 2200 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።

ባለፈው ሳምንት ሳባሪማላ የተባለው ቤተ እምነት ውስጥ ሴቶች መግባት አይችሉም ብለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አመጽ ማስነሳታቸው ይታወሳል።

አሜሪካ

• በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ በሰው ሰራሽ ማሽን የተሰራ አንድ ስዕል 432 ሺ ዶላር ተሸጠ።

ከዚህ በፊት የተሳሉ 15 ሺ ስዕሎችን በማቀላቀል የተሰራው የጥበብ ውጤት ኤድሞንድ ቤላሚ የሚል ስያሜ አግንቷል።

• ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 48 ሠራተኞቹን ከወሲብ ቅሌት ጋር በተያያዘ ማባረሩን ገለጸ።

ከተሰናበቱት ሰራተኞች አንዱ የሆነው አንዲ ሩበን ደግሞ መሥሪያ ቤቱን ሲለቅ 90 ሚሊዮን ዶላር የስንብት ገንዘብ ወስዷል ተብሏል።

• ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የዶናልድ ትራምፕ የግል ስልክ በቻይናና ሩሲያ ሳይጠለፍ አይቀርም የሚል ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

ቻይናና ሩሲያ በበኩላቸው ዜናውን መሰረተቢስ በማለት አጣጥለውታል።

እንግሊዝ

• ለንደን ውስጥ ለአርኪዮሎጂካዊ ጥናት በሚል 45 ሺ የሰዎች አጽም ከመቃብር ስፍራ ሊነሳ ነው።

ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ስፍራነት ሲያገለግል የነበረው ቦታ መነካት የለበትም በማለት አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውመውታል።

ግሪክ

• የግሪኳ ዛኪንቶስ ደሴት 6.4 ማግኒቲዩድ በተለካ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታች።

የመሬት መንቀጥቀጡ እስከ 50 ኪሎሜትር ድረስ የተሰማ ሲሆን፤ ነዋሪዎች የቤት መደርመስን በመፍራት ምሽቱን በመንገዶች ላይ አሳልፈዋል።