ቀኝ ዘመሙ እና አክራሪው ቦልሶናሮ የብራዚል ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ

ቀኝ ዘመሙ ቦልሶናሮ የብራዚል ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቀኝ ዘመሙ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ጃይር ቦልሶናሮ በጉጉት የተጠበቀውን የብራዚል ምርጫ ማሸነፍ ችለዋል።

ቦልሶናሮ 55.2 በመቶ ድምፅ በማምጣት ነው ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የነበሩት የሰራተኞች ፓርቲው ፈርናንዶ ሃዳድን መርታት የቻሉት።

«ሙስናን ነቅዬ አጠፋለሁ፤ በሃገሩ የተስፋፋውን ወንጀልም እቀንሳለሁና ምረጡኝ» ሲሉ ነበር ቦልሶናሮ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የሰነበቱት።

የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱ በጣም ከፋፋይ እንደበር ብዙዎች የተስማሙበት ሲሆን ሁለቱም ወገኖች 'አጥፊ' እየተባባሉ ሲወቃቀሱ ከርመዋል።

ወግ አጥባቂው ሚሼል ቴሜር በሙስና ምክንያት ከሥልጣን በወረዱት ዴልማ ሩሴፍ ምትክ ብራዚልን ላለፉት ሁለት ዓመታት ቢያስተዳድሩም ህዝቡ ዓይንዎትን ለአፈር ብሏቸዋል።

ከጠቅላላ ህዝብ 2 በመቶ ብቻ ተወዳጅነት ያገኙት ቴሜር አሁን ሥልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል።

ተቀናቃኛቸውን በ10 በመቶ ድምፅ የረቱት ቦልሶናሮ ለሃገራቸው ህዝብ ለውጥ ለማምጣት አማልክትን ጠርተው ምለዋል።

«ዲሞክራሲን ጠብቄ አስጠብቃለሁ፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ የሃገራችንን ዕጣ ፈንታ አብረን እንቀይራለን» ሲሉም ቃላቸውን ሰጥዋል አዲሱ መሪ።

የአዲሱ ተመራጭ ቦልሶናሮ ተቃዋሚዎች ግን ሰውየው ያለፈ ሕይወታቸው ከውትድርና ጋር የተያያዘ ስለሆነ ረግጥህ ግዛ እንጂ ዲሞክራሲ አያውቁም ሲሉ ይወርፏቸዋል።

ቦልሶናሮ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያሰሟቸው የፆታ ምልክታን፣ ሴቶችን እንዲሁም ዘርን አስመልክተው የሰጧቸው አጫቃጫቂ አስተያየቶችም ያሳሰቧቸው አልጠፉም።

ዋነኛው ተቀናቃኝ ፈርናንዶ ሃዳድ በበኩላቸው ድምፁን ለእኔ የሰጠው ሕዝብ አደራ አለብኝ ብለዋል፤ በተቃዋሚ ፖለቲከኛነት እንደሚቀጥሉ ፍንጭ በመስጠት።

ብራዚል በፈረንጆቹ 2000-2013 ባሉት 13 ዓመታት ያክል በግራ ዘመም የሰራተኞች ፓርቲ ስትመራ ብትቆይም አሁን ግን ወደ ቀኝ ዘማለች።