የማንነት ጥያቄዎች የጎሉበት የአማራ ክልል ከተሞች ሰልፍ

በባህርዳር የተደረገው ሰልፍ በከፊሊ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media Agency

በባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን በሰልፎቹ ላይ "የወልቃይት እና የራያ የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል፤ ለጣናና ለላልይበላ አፋጣኝ ትኩረት ይሰጥ" የሚሉ መፈክሮችም በከፍተኛ ሁኔታ የታዩበት ነው።

ሰልፎቹ በባህርዳር፣ በደሴ፣ በደብረ ብርሃን፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር ፣ ወልድያ፣ ሰቆጣ፣ ላልይበላ ተካሂደዋል።

ሰልፎቹ በሰላም እንደተጠናቀቁ የተዘገበ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም በሰሞኑ አላማጣ ከተማ የማንነት ጥያቄን ባነሱና የፀጥታ ኃይሎችጋር በተፈጠረ ግጭት አምስት ሰዎች መሞታቸውንም በማስመልከት፤ መብታቸውን ስለጠየቁ በዜጎች ላይ ጥቃት ሊደርስባቸውም አይገባም የሚሉም መልዕክቶች ተላልፈዋል።

ሰልፈኞቹ በማንነት ጥያቄ ምክንያት የሚደርሱ ግፎች እና በደሎች ሊቆሙ ይገባል በሚልም መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ የአማራ ክልል የዞን ከተሞች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ የገለፁበት እንደሆነም የሰልፉ አስተባባሪዎችን በመጥቀስ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ላይ ጎልቶ ያታየው የማንነት ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ሲሆን በተጨማሪም ለአደጋ ተጋልጠዋል ስለተባሉት የክልሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶች ስለሆኑት ላልይበላና ጣና ሃይቅን ለመታደግ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በደብረ ብርሃን በነበረው ሰልፍ ላይ አስተባባሪው ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት "አማራ በአማራነቱ የሚሸማቀቅበት ምንም ሁኔታ ሊኖር አይገባም፤ የሰሜን ሸዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ከወልቃይት እና ከራያ ህዝብ ጎን መሆናችን ለመግለፅ እወዳለሁ" በማለት አቶ አማረ መልዕክት እንዳስተላለፉ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

በክልሉ መዲና ባህርዳር ላይ በነበረው ሰልፍ የተለያዩ ጥያቄዎችን የተንፀባረቁ ሲሆን ለጣና ሐይቅና ለላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የፌዴራል መንግሥትን ትኩረት እንዲሰጥ፣ የማንነት ጥየቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ መሻሻል እንዲደረግና፣ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የሚደረገው የጥላቻ ዘመቻ አንዲቆምና የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ ከአማራ ሕዝብ ጎን እንዲቆም የሚጠይቁ ናቸው።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ ዓለሙ‹‹ያስተላለፋችሁትን መልዕክት ለሚመለከተው አካል ማድረስ ብቻ ሳይሆን ለተፈፃሚነቱ ከጎናችሁ ሆነን እንደምንሠራ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ›› እንዳሉ የክልሉ መገኛኛ ብዙሃን ተዘግቧል።

በተያያዘም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት ወደ አማራ ክልል ተጉዘው የሰልፈኞቹ ዋነኛ ትኩረት ከሆኑት መካከል በአደገኛ ወራሪ አረም አደጋ ላይ የወደቀውን የጣና ሃይቅንና አፋጣኝ ጥገና የሚፈልጉትን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተው መንግሥት አስፈላጊውን ነገር እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።