የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል ፖለቲካ በቃኝ ማለታቸውና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የጀርመን መርሔተ መንግስት አንጌላ መርክል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የጀርመን መርሔተ መንግስት አንጌላ መርክል

ኢትዮጵያ

በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ዛሬ ኢትዮጵያ ገቡ።

የቀድሞው ሚኒስትር ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫም የደርግን አገዛዝ በመቃወም ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለቀው ላለፉት 32 ዓመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

***

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አብዲ መሀመድ ዑመርና በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ቀን ሰጠ።

የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናቱ፤ በተጠረጠሩበት የማፈናቀል፣ የአካል ጉዳትና ህወይት ማለፍ ወንጀል ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀን ፈቅዷል።

ኤርትራ

ኤሪ ሳት የተሰኘ አዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሳተላይት ስርጭቱን ዛሬ ጀመረ። የቴሌቪዥን ጣቢያው ከኤርትራ ውጪ የተቋቋመ የመጀመሪያ ጣቢያ ነው ተብሏል።

ተቀማጭነቱን ጀርመን ያደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያው በትግርኛ፣ በአፋርኛና በአረብኛ ቋንቋ ስርጭቱን እንደሚያስተላልፍ ታውቋል።

ኬንያ

የኬንያ አየር መንገድ ከመዲናዋ ናይሮቢ ወደ ኒዮርክ አሜሪካ የቀጥታ በረራ ጀመረ።

ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የቀጥታ በረራው በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ፣ የቱሪዝምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ያጠናክራል ብለዋል።

ዛምቢያ

በዛምቢያ ሰሜናዊ አካባቢ በ5, 655 ካራት የሚለካ፣ ጥራት ያለውና 1.13 ኪሎግራም የሚመዝን የከበረ ማዕድን መገኘቱ ተገለፀ።

ካገም የተባለው የማዕድን አውጭ ድርጅት እንዳስታወቀው 'ኢንካላሙ' የተባለው ይህ ማዕድን ወርቃማ አረንጓዴ ቀለም አለው።

ጋቦን

በጋቦን ከ70 በላይ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ይፋዊ ድረ ገፆች ባልታወቁ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድኖች እጅ መውደቁ ተነገረ።

ከእነዚህ መካከል የአገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ እና የኮሚዩኒኬሽን ሚንስቴር መስሪያቤት ድረ ገፆች ይገኙበታል ተብሏል።

ቱኒዚያ

በቱኒዚያ ዋና ከተማ ቱኒስ አንዲት የ30 ዓመት ሴት በራሷ ላይ ያጠመደችው ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ 8 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።

ከፍንዳታው ጀርባ ማን እንዳለ የታወቀ ነገር ባይኖርም የሽብር ተግባር ሳይሆን አንደማይቀር ተገምቷል።

ሴትዮዋ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ወታደራዊ ዳራ እንዳልነበራት ተገልጿል።

ጀርመን

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል በአውሮፓውያኑ 2021 በሚካሄደው ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታወቁ።

ለ18 ዓመታት ከመሩት ፓርቲያቸው (ሲዲዩ) መሪነታቸውም በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚለቁ ተናግረዋል።

የስልጣን ዘመኔ ከተጠናቀቀ በኋላ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አንቅስቃሴ አልፈልግም ሲሉም ተደምጠዋል።

ኢንዶኔዥያ

188 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ የሁሉንም ተሳፋሪዎች ህይወት ሳይቀጥፍ አይቀርም ተባለ።

ላይነ የተባለው የኢንዶኔዢያ የመንገደኞች አውሮፕላን ከዋና ከተማዋ ጃካርታ ተነስቶ ከ 11 ደቂቃዎች የአየር ላይ ቆይታ ነበር ባህር ላይ የተከሰከሰው።

እስካአሁን በህይወት የተረፉ ሰዎች ስለመኖራቸው ምንም ፍንጭ አልተገኘም።

እንግሊዝ

የሌስተር ሲቲው ባለቤት የግል ሄሊኮፕተራቸው ከኪንግ ፓወር ስታዲየም ሲወጣ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ መሞታቸው ተሰምቷል።

ቢሊዬነሩ፣ ሁለት ሰራተኞቹ፣ ዋና አብራሪና አንድ ተሳፋሪ ሄሊኮፕተሯ ስትከሰከስ ወዲያው መሞታቸው ተረጋግጧል።

ይህንን ተከትሎም የሌስተር ሲቲ ተጫዋቾች ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው።

አውሮፓ

የአውሮፓውያን የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ የአየር ብክለት በአውሮፓ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ አስታወቀ።

ከሶስት ዓመታት በፊት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአየር ብክለት ሳቢያ በዓመት ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ያለጊዜያቸው ይሞታሉ።