በእንግሊዝና በጋምቢያ የሚገኙ ተመራማሪዎች ውሾች ወባን በማሽተት እንደሚለዩ አስታወቁ

ውሻ

የፎቶው ባለመብት, Once Upon a Pixel

ውሾች በአፍንጫቸው የማሽተት ችሎታ ብቻ የወባ በሽታን መለየት እንደሚችሉ በእንግሊዝና በጋምቢያ የሚገኙ ተመራማሪዎች አስታወቁ።

አጥኚዎቹ በወባ በሽታ የተጠቃ ሰው ልብስ ለውሾቹ በማስሸተት ለረጅም ወራት አሰልጥነዋቸዋል።

በተለይ በአፍሪካና በእስያ በየዓመቱ የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚቀጥፈው የወባ በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት በሚደገረው አለምዓቀፍ ርብርብ ይሄኛው ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ምንም እንኳን የምርምር ውጤቱ ገና በሙከራ የሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ የወባ በሽታን ለመርመር እንደ አዲስ መንገድ ሊያገለግል ይችላል።

ጥናቶች እንሚያሳዩት በወባ በሽታ ስንጠቃ የሰውነታችን ጠረን የሚቀየር ሲሆን፤ የወባ ትንኞች ደግሞ በዚህ ጠረን ስለሚማረኩ የተጠቂውን ሰው ደም ቀድመው በመምጠጥ በሽታውን ያስተላልፋሉ።

አሁን ደግሞ ውሾች ይህንን ጠረን በማሽተት በሽታውን መከላከል ይችላሉ።

የተመራማሪዎቹ ቡድን በጋምቢያው 'አፐር ሪቨር' ክልል የሚገኙ ህጻናት የለበሷቸውን ካልሲዎች አሰባስበው ወደ እንግሊዝ በመላክ ነው ጥናቱ የተጀመረው።

ከተላኩት 175 ካልሲዎች ደግሞ 30 የሚሆኑት በወባ በሽታ የተጠቁ ህጻናት የለበሷቸው ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, LSHTM

ምንም እንኳን ውሾቹ አብዛኛውን በበሽታው የተጠቁ ህጻናትን ካልሲዎች ቢለዩም፤ ከአስር ህጻናት አንዱ በሽታው ሳይኖርበት እንደ ተጠቂ ቆጥረውታል።

ይሄ ደግሞ ውሾቹን እስከመጨረሻው ከማሰልጠን ጋር የተያያዘ ነው።

የተመራማሪ ቡድኑ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቲቭ ሊንዲሴይ በጥናቱ ውጤታማነት እጅግ መደሰታቸውንና ለጊዜው ውሾቹ የምርመራ አገልግሎት ላይ እንደማይውሉ ገልጸዋል።

ውሻዎቹ በሽታውን ሙሉ በሙሉ መለየት የሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ የማሰልጠን ስራው እንደሚቀጥልና፤ ሌሎች በሽታዎችንም መለየት እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚሰሩ ፕሮፌሰር ስቲቭ ጨምረዋል።

በሙከራ ደረጃም በአየር መንገዶችና ሌሎች ሰዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች ውሻዎቹን በማሰማራት ውጤታማኑትን ለመፈተሽም ታስቧል።