በቱኒዝያ በደረሰ ጥቃት አንዲት ሴት ራሷን በቦምብ አፈነዳች

በቱኒዝያ የደረሰው ፍንዳታ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በቱኒዝያዋ መዲና ቱኒስ የ30 ዓመት ዕድሜ ያላት አንዲት ሴት በቦምብ ራሷን በማፈንዳቷ ዘጠኝ ሰዎች መጎዳታቸውን የቱኒዝያ የኃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል።

ፍንዳታውን ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢገልፁም ሴትዮዋ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ስልጠና እንደሌላት አስታውቀዋል።

የከተማዋ ማዕከል በሆነው ሐቢብ ቦርጉይባ ተብሎ በሚጠራው ጎዳና በደረሰው ፍንዳታም የተጎዱት ስምንቱ ግለሰቦች ፖሊስ መሆናቸው ተገልጿል።

እስካሁን ድረስ ሞት ያልተከሰተ ሲሆን፤ ለጥቃቱም ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።

ይህ ጥቃት የተፈፀመው ከሶስት ዓመት በፊት በደረሱ ክፉኛ የሽብር ጥቃቶች ተሽመድምዶ የነበረው የሃገሪቱ ኢንዱስትሪ እያንሰራራ በነበረበት ወቅት ነው ።

በአውሮፓውያኑ 2015 ባርዶ ሙዝየም በደረሰ ጥቃት 22 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ በዛው ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ በአንድ መዝናኛ ቦታ 38 ሰዎች ተገድለዋል።

የአሁኑ ጥቃት የደረሰው ከፈረንሳይ ኤምባሲ 200 ሜትር ርቀትና የኃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒሰቴር በሚገኝበት ጎዳና መሆኑን የሀገሪቱ ጋዜጠኛ ሱሐይል ክሚራ ለቢቢሲ ገልጿል።

ፍንዳታው ከደረሰ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሲሆን ቦታው የደረሰው ጋዜጠኛ ከፍተኛ የሆነ ጥቁር ጭስም አካባቢውን ሸፍኖት ነበር ብሏል።

ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ሱቆች የተዘጉ ሲሆን ፖሊስም መንገዱን ዘግቷል።

በአውሮፓውያኑ 2015 አጥፍቶ ጠፊ 12 የፀጥታ ኃይሎችን ከገደለ በኋላ ቱኒዝያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንደነበረች የኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እስከ ህዳር መጀመሪያ ላይ እንዲራዘም መወሰኑን የዜና ወኪሉ ኤኤፒ አስታውቋል።