በኬንያ የልጃገረዶች ት/ቤት ሴት መስሎ የገባው ተማሪ መታሰሩን የተመለከቱና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የሙዚቃ መሳሪያዎች

ኢትዮጵያ

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ መንግሥት የሕዝቡን ደህንነትና ሕገ-መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን እንደማይታገስ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኦቢኤን በሰጡት መግለጫ በኦነግ ስም ሕዝቡን ለችግር እየዳረገ ያለ አካል በአፋጣኝ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ አስጠንቅቀዋል።

ሶማሊያ

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (ሲፒጄ) ሶማሊያ ከዓለማችን ለጋዜጠኞች አደገኛ የሆኑ አገራት ተርታ መደበ።

ይህ የሆነው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኣብዱላኢ ሚሬ ሃሺ የተባለ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ መገደሉን ተከትሎ ነው።

ለግድያው የመንግስት ኃይሎችና የአልሻባብ ታጣቂዎች እጅ አለበት ተብሏል።

ኡጋንዳ

በኡጋንዳ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የወጣው የስደተኞች ቁጥር በ300 ሺህ ተጋኗል ተባለ።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት እና የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ በጋራ ባወጡት መግለጫ ቁጥሩ የገዘፈው አንድ ስደተኛ ከአንድ በላይ ጣቢያዎች በመመዝገቡ እንዲሁም በትክክል የተመዘገቡትም ድንበር ተሻግረው በመሄዳቸው ነው ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ

በደቡብ አፍሪካ ምዕራብ ኬፕ ግዛት በአንድ ታዋቂ መናፈሻ በተነሳ የሰደድ እሳት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሞቱ።

ከሟቾቹ መካከል የ8 ወር ነፍሰጡር ሴትና ሶስት ህፃናት ይገኙበታል።

እሳቱን ለመቆጣጠር የሚነፍሰው ከባድ ነፋስ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረዋል።

ኬንያ

በኬንያ ለሌላ ተማሪ የሙዚቃ ፈተና ለመፈተን ሲል የሴት የደንብ ልብስ ለብሶ በልጃገረዶች ት/ቤት የገባ ተማሪ ለእስር ተዳረገ።።

የት/ቤቱ ርዕሰ መምህርና የሙዚቃ አስተማሪውም ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል።

ካናዳ

ካናዳዊቷ እናት ከ31 ዓመት በኋላ ከልጇ ጋር ለአይነ ስጋ በቁ።

ሁለት ዓመት ሳይሞላው በገዛ አባቱ ተሰርቆ በሃሰተኛ ስም በአሜሪካ እየኖረ ሳለ ነበር ሀሰተኛ መረጃው ሲጋለጥ በህይወት እንደሌለች ከተነገረው እናቱ ጋር ለመገናኘት የበቃው።

ህንድ

በህንድ የዶርዳርሻን ብሔራዊ ሚዲያ ጋዜጠኛ እንዲሁም ሁለት ፖሊሶች በማኦይስት ታጣቂዎች ተገደሉ።

ግድያው የተፈፀመባቸው በቀጣይ የሚካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ባመሩበት ወቅት በመኪናቸው ላይ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ነበር።

ጣሊያን

በጣሊያን በሰዓት 180 ኪሎ ሜትር በሚምዘገዘግ አውሎ ነፋስና ከባድ ዝናብ ሳቢያ ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

በምዕራብና በሰሜን ግዛትም ትምህርት ቤቶችና የጎብኝዎች መዳረሻም ዝግ ሆነዋል።

ቻይና

ቻይና ለ25 ዓመታት እገዳ ጥላበት የነበረውን የ አውራሪስ ቀንድና የነብር አጥንት ንግድን አነሳች።

ድርጊቱ የዱር እንስሳት ተሟጋቾችን ያስቆጣ ቢሆንም ለምርምርና ለመድሃኒትነት አገልግሎት ለማዋል ስትል እንደሆነ አስታውቃለች።

አሜሪካ

አሜሪካ በሜክሲኮ በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ለመከላከል ከ 5 ሺህ በላይ ወታደሮቿን አሰማራች።

ፕሬዚደንት ትራምፕ "ስደተኞች ወደ አሜሪካን ለመውረር ቢሞክሩ የሚያገኙት ወታደሮቹን ነው" ሲሉ ወርፈዋል።

ጀርመን

ኒየልስ ሆግል የተባለው የ41 ዓመት ጀርመናዊው ነርስ 100 የሚሆኑ በሽተኞችን አውቆ ገድሏል በሚል ክስ ተጠርጥሮ ለፍርድ ሊቀርብ ነው።

ግለሰቡ በሥራ ላይ ሳለ ባጠፋው ሕይወት ምክንያት የዕድሜ ልክ እሥራት ላይ ይገኛል።