ኢትዮጵያ ጂ-20 ኮምፓክት የተባለውን ቡድን ተቀላቅላለች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና መራሂተ መንግሥት አንግላ ሜርክል

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega/Twitter

ጂ-20 ይሉታል በእንግሊዝኛው አጠራር፤ ቡድን 20 የአማርኛ አቻ ፍቺው ነው፤ 20 የዓለም ሃገራትን ያቀፈው ቡድን።

ልዕለ ሃያላኑ አሜሪካ፣ ቻይና እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች 16 የዓለማችን ሃገራትን እና አውሮፓ ሕብረት የቡድኑ አባላት ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2008 ምሥረታውን ያደረገው ይህ ቡድን የየሃገራቱን ማዕከላዊ ባንኮች በማስተባበር ለምጣኔ ሃብታዊ መጠናከር የሚሠራ ነው።

ሃገራቱ ከራሳችን አልፎ ለመላው ዓለም የምጣኔ ሃብት መረጋጋትም እንሠራለን ይላሉ።

ካናዳ እና አሜሪካ ከሰሜን፤ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲናና ብራዚል ከደቡብ አሜሪካ፤ ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ፣ ህንድ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ከእስያ፤ ፈረንሳይ፣ ቱርክ፣ ጀርመን እና ጣልያን ከአውሮፓ፤ ብቸኛዋ የአፍሪቃ ተወካይ ደቡብ አፍሪቃና አውስትራሊያ አባል ሃገራት ናቸው።

እኒህ የምድራችን ሁለት ሦስተኛ ህዝብ የሚኖርባቸው 19 ሃገራት የዓለማችንን ጠቅላላ ምርት 85 በመቶ እንዲሁም የዓለም ንግድን 80 በመቶ ይይዛሉ።

ኢትዮጵያ እና ጂ-20

ኢትዮጵያ እና ጂ-20 ወዳጅነታቸው የሩቅ ዘመድ ዓይነት ነበር፤ አልፎ አልፎ ኢትዯጵያ ስብሰባውን በእንግድነት ከመታደም ያለፈ ሚና አልነበራትም።

የዘንድሮ መዳረሻውን ከአባላቱ አንዷ በሆነችው ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው የቡድኑ ስብሰባ ግን አንድ ሃሳብ ብልጭ ብሎለታል። ለምን የጂ-20 የአፍሪካ ክንፍ አናቋቁምም? የሚል።

በጀርመኗ መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የተጠነሰሰው ይህ ውጥን ጂ-20 ኮምፓክት ከአፍሪቃ ጋር የተሰኘ ስያሜ ተሰጥቶታል።

አላማውም የግል ኢንቨስትመንትን አህጉረ አፍሪካ ውስጥ ማነቃቃትና እና ማስተዋወቅ ይሆናል።

ማዕቀፉ፤ አፍሪካ ውስጥ የጋራ ንግድ ቢበረታታ እና የገንዘብ ተቋማት ራሳቸውን ቢችሉ ትልቅ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነትን አንግቦ ተነስቷል።

ለውጥ ለማምጣት ቆርጠው የተነሱ የአፍሪካ ሃገራት ከዋናው የጂ-20 አባላት ጋር ምጣኔ ሃብታዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት መንገድ እንደሚሆንም ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ፣ ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ እና ቱኒዚያ የክንፉ የመጀመሪያ አባልነት መታወቂያ የተሰጣቸው ሃገራት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአውሮ

አውሮፓ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ከፈረንሳይ ጉብኝታቸው በኋላ ያቀኑት ወደ ጀርመን ነው፤ በዚህ የምሥረታ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ።

«የጂ-20 ሃገራት ውስጥ ያለው ዓይነት ኢንቨስትመንት እኛም ማየት እንሻለን፤ ይህ ክንፍ በዚህ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተስፍ እናደርጋለን» ብለዋል በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍፁም አረጋም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኮንፈረሱ ላይ ተገኝተው ስለኢትዯጵያ ንግግር እንዳደረጉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega/Twitter

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት የተገኙበት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ኢትዮጵያ ለኢንቨስተሮች ምን ልታቀርብ እንደምትችል ያሳየችበት ነበርም ተብሏል።

«ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሆነ የኢንቨስትመንት አማራጭ አላት፤ ይህን ዕድል ተጠቅሜ ስትራቴጂክ የሆኑ አማራጮችን ማቅረባችንን ልገልፅላችሁ እወዳለሁ» ብለዋል መንበረ ሥልጣን ከጨበጥ መንፈቅ ያለፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ።

በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች እየናጧት የምትገኘው ኢትዮጵያን ጨምሮ የዚህ ክንፍ አባል የሆኑ ሃገራት በበርከታ መንገዶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

ከጥቅሞቹ አንዱ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የጂ-20 አባል ሃገራት ከሌሎች ሃገራት በበለጠ ለክንፉ አባላት ቅድሚያ መስጠታቸው ነው።

አልፎም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ቴክኒካዊ እርዳታ ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ ማዕቀፉ በግለፅ ያስቀምጣል።

ከ20ዎቹ ሃገራት ኢንቨስት ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የግል ባለሃብቶች ወደእነዚህ 11 የአፍሪካ ሃገራት እንዲሄዱ መበረታታቸው ደግሞ ሌላኛው ጥቅም ተደርጎ ተቀምጧል።

2017 ላይ የተመሠረተው ይህ ክንፍ ምንም እንኳ አስካሁን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ባያመጣም ለሃገራቱ ምጣኔ ሃብት መጠናከር የበኩሉን እንደሚያበረክት እምነት ተጥሎበታል።

ከኢንቨስትመንት በፊት ሰላም ይቀድማል የሚል ትችት ያላጣት ኢትዮጵያስ ከዚህ ክንፍ አባልነት የምታተርፈው ምን ይሆን?. . . በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።