ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰችው የቱኒዝያ አጥፍቶ ጠፊ ስራ የሌላት ምሩቅ እንደሆነች ተገለፀ

በቱኒዝያ መዲና ቱኒዝ ፖሊሶች የቦምብ ፍንዳታውን ሲመረምሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በቱኒዝያ መዲና ቱኒስ በደረሰው የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ ዘጠኝ ግለሰቦች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ ባለስልጣናቱ የአፈንጂዋን ማንነት ይፋ አድርገዋል።

ማሂዳ ተብላ ከምትጠራው ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የመጣችው የሰላሳ ዓመት ዕድሜ ያላት ሙና ጉባ ስራ የሌላት ምሩቅ እንደሆነች የአቃቤ ህግ ቢሮ አስታውቋል።

የቦምብ ጥቃቱን ያደረሰችው ሙና አባት በበኩላቸው ይህንን ጥቃት በፍቃደኝነት አድርሳዋለች የሚለውን ይጠራጠራሉ።

ፖሊስን ጠቅሶ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደዘገበው ሰውነት ላይ የሚጠለቀውን ቦምብ ሳይሆን ቤት ውስጥ የተሰራ ቦምብ ተጠቅማለች ብሏል።

እንግሊዝኛ ቋንቋን ያጠናችው ሙና ከተመረቀች ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ ቤተሰቦቿንም ለመደገፍ በጎችን ትጠብቅ እንደነበር ተገልጿል።

በቱኒዝያ ስራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋ ሲሆን፤ 1/3ኛ የሚሆነው ህዝብም ስራ የላቸውም።

"እንዲህ አይነት ነገር ለመፈፀም ሀሳቡ ይኖራታል ብየ አላምንም" በማለት አባቷ መሀመድ ጉቤላ መናገራቸውን ኤኤፍፒ በዘገባው አስቀምጧል።

የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ሂቸም ፉራቲ በበኩላቸው ጥቃቱ የደረሰው በአንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን ተናግረው፤ ሙና ፅንፈኞች ዝርዝር ውስጥም ሆነ ከአክራሪ አማኞች ጋር ግንኙነት እንዳላትም እንደማይታወቅ አስረድተዋል።

የትኛውም ቡድን ቢሆን ለጥቃቱ ኃላፊነት ያልወሰደ ቢሆንም የሀገሪቱ ሚዲያ ሙና ፅንፈኛ ዝንባሌ ሳይኖራት እንዳልቀረ ዘግበዋል።

በመዲናዋ ቱኒስ ሁኔታዎች በትናንትናው ዕለት ወደ ሰላም የተመለሱ ሲሆን ፖሊስ አካባቢውንም ተቆጣጥሮት ነበር።

ባለስልጣኖች በበኩላቸው በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት እንደሌለ ገልፀዋል።