የፓኪስታን ፍርድ ቤት ሞት የተፈረደባትን ክርስቲያን ነፃ ለቀቀ

አሲያ ቢቢ

በእስልምና ሃይማኖት ላይ ስድብ ሰንዝረሻል ተብላ ሞት ተፈርዶባት የነበረችው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በፓኪስታን የሚገኝ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣቱ እንዲነሳላት ወሰነ።

አሲያ ቢቢ የተባለችው ሴት በአውሮፓውያኑ 2010 ነበር ከጎረቤቶቿ ጋር ስትጣል ነብዩ ሞሃመድን ተሳድበሻል ተብላ ክስ የተመሰረተባት።

ምንም እንኳን ጥፋተኛ እንዳልሆነች በተደጋጋሚ ብትገልጸም፤ ያለፉትን ስምንት ዓመታት በእስር ቤት ነበር ያሳለፈችው።

ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው በሞት አትቀጣም፤ እንደውም በነጻ ትሰናበት የሚለው ውሳኔ ደግሞ በፓኪስታን የሚገኙ ብዙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን አስቆጥቷል።

ውሳኔውን የተቃወሙ ፓኪስታናውያን ካራቺ፣ ላሆር፣ ፔሽዋርና ሙልታን በተባሉ ከተማዎች ሰልፍ የወጡ ሲሆን ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው እንደነበረም ተገልጿል።

በዋና ከተማዋ ኢዝላማባድ የሚገኘው ውሳኔውን ያስተላለፈው ፍርድ ቤት በር ላይ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተሰብስበው ወደ ውስጥ እንዳይገቡ በፖለስ እየተጠበቁ ነው።

የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉት የነበሩት ዋና ዳኛ ውሳኔያቸውን ለተሰበሰቡት ሰዎች ሲያነቡ ''አሲያ ቢባ ከዛሬ ጀምሮ ሌላ የሰራችው ወንጀል ከሌለ ሼኩፑራ ውስጥ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት ያለምንም ችግር መውጣት ትችላልች'' ብለዋል።

ምንም እንኳን ውሳኔው ሲሰጥ በፍርድ ቤቱ መገኘት ባትችልም፤ አሲያ ቢቢ ከማረሚያ ቤት ሆና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እስካሁን ድረስ ለማመን እንደከበዳት ተናግራለች።

''የሰማሁትን ነገር ማመን አልችልም፤ አሁኑ ከእስር ቤት መውጣት እችላለሁ?'' ብላለች።

የዛሬ ስምንት ዓመት አሲያ ከጎረቤቶቿ ጋር በመሆን ፍራፍሬ ለመሰብሰብ ወጣ ይላሉ። ታዲያ ከስራ በኋላ እሷ የነካችውን የውሃ መቅጃ መጠቀም እንደማይፈልጉ ጎረቤቶቿቸ ይነግሯታል። ለምን ብላ ብትጠይቅ በሃይማኖትሽ ምክንያት ውሃ መቅጃው ቆሽሿል ይሏታል።

በመቀጠልም ሃይማኖቷን መቀየር እንደለባት ሲነግሯት አጸያፊ የሆኑ ስድቦችን መሰንዘሯን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባታል።

ወደ ቤቷ ስትመለስም ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባትና በጊዜው ወንጀል መፈጸሟን በማመኗ ለፖሊስ ተላልፋ ተሰጥታለች።

የአሲያ ጠበቃ በውሳኔው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ለደንበኛቸው ደህንነት ግን አሁንም እንደሚፈሩ ገልጸዋል። ምክንያቱም ውሳኔውን የሰሙ ሰዎች በፍርድ ቤቱ አቅራቢያ በመሰባሰብ መሞት እንዳለባት ሲናገሩ ነበር።

አሲያ ወደ ማረሚያ ቤት እንደገባች የፍርድ ሂደቱ ትክክል አይደለም ብለው የተከራከሩት የፑንጃብ ግዛት አስተዳዳሪ ሳልማን ታሲር በሰው ተገድለዋል። እሳቸውን የገደለው ሰውም የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ተገድሏል።

ገዳዩ ሙምታዝ ቃድሪ ከተገደለ በኋላ የአካባቢው ሰዎች ጀግናችን ነው በማለት በስሙ የጸሎት ቦታ ሰርተውለታል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልጇና ቤተሰቦቿ ለደህንነቷ ስለሚያሰጋት ከፓኪስታን ለቅቃ መሄድ እንዳለባት እየተናገሩ ነው። ከተለያዩ ሃገራትም የጥገኝነት ፍቃትድ እንደተሰጣት ተገልጿል።