ትራምፕ አሜሪካ ለተወለዱ ልጆች የምትሰጠውን ዜግነት ለማስቀረት እየጣሩ ነው

በአሜሪካ የተወለዱ ህፃናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተለያዩ ምክንያቶች ተሰደው ወደ አሜሪካ የገቡ ሰዎች የመኖሪያም ሆነ የዜግነት መብት ባያገኙ እንኳን አሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ልጆቻቸው በቀጥታ የአሜሪካ ዜግነትን ያገኛሉ።

ከዚህ አልፎም ለጉብኝትም ሆነ ለህክምና ወደ አሜሪካ የሄደች እናት በቆይታዋ ወቅት ልጇን ከወለደች ፍላጎቱ ካላት ልጇ የአሜሪካ ዜግነት እንድታገኝ/እንዲያገኝ ማድረግ ትችላለች። ለዚህም አቅሙ ያላቸው የእኛ ሃገር እናቶችን ጨምሮ በርካቶች መውለጃ ጊዜያቸው ሲቃረብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንደሚያቀኑ ይነገራል።

አሁን ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከ150 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ህገ መንግሥት አንቀጽ 14 ላይ የሰፈረው ማንኛውም በአሜሪካ ምድር ላይ የተወለደ ሰው ዜግነት ያገኛል የሚለውን ህግ ለማስቀረት እየሰሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።

"ህጉን ለመቀየር ሃሳቤን ሳቀርብ ሁሌም ህገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ይሉኛል፤ እኔ ደግሞ እንደውም ምንም ማሻሻል አያስፈልገውም ባይ ነኝ'' ብለዋል።

"በተጨማሪ ምክር ቤቱ ካጸደቀው መቀየር እንደሚቻል ነግረውኝ ነበር፤ ነገር ግን በፕሬዝዳንቱ ቀጥተኛ ትዕዛዝም መቀየር እንደሚቻል ተነግሮኛል።"

ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት ደግሞ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል። ሰዎችም እንዲህ አይነት አከራካሪ የህገ መንግሥቱን ክፍል ፕሬዝዳንቱ በቀጭን ትዕዛዝ መቀየር ይችላሉ ወይ? በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

1. በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ምንድነው?

የአሜሪካ ህገ መንግሥት አንቀጽ 14 የመጀመሪያ አረፍተ ነገር በመወለድ ስለሚገኝ ዜግነት ያትታል።

''ማንኛውም አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ወይም ተገቢውን ግዴታዎች የተወጣ ሰው የአሜሪካ ዜጋ የመሆን ሙሉ መብት አለው'' ይላል።

የስደተኞች ወደ አሜሪካ መጉረፍ ያሳሰባቸው ሰዎች ህጉ የህገ ወጥ ስደተኞች 'ማግኔት' ነው በማለት ማንኛዋም ሴት አሜሪካ መጥታ መውለድን የሚያበረታታው ህግ እንዲቀር ይከራከራሉ።

እንደውም አብዛኛዎቹ እናቶች በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ በመግባት ነው ልጆቻቸውን የሚወልዱት። የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች ህጉን የወሊድ ቱሪዝም የሚል ስም ሰጥተውታል።

"የሚወለዱት ህጻናት ቢያንስ ለ85 ዓመታት ከነሙሉ ጥቅማጥቅሞቹ የአሜሪካ ዜጋ ሆነው ይቆያሉ፤ ይህ የማይሆን ነገር ነው'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ፒው የተባለ የምርምር ማዕከል በአውሮፓውያኑ 2015 በሰራው አንድ ጥናት መሰረት 60 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ህጉን የሚደግፉ ሲሆን፤ 37 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህጉ መቀየር አለበት ባይ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

2. አሜሪካ ውስጥ በመወለድ የሚገኝ ዜግነት መነሻው ምንድነው?

ስለጉዳዩ የሚያወራው አንቀጽ 14 በአሜሪካ ህገ መንግሥት ውስጥ የተካተተው በአውሮፓውያኑ 1868 ልክ የእርስ በርስ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ነበር።

አንቀጽ 13 የባሪያ ንግድን በ1865 ሲከለክል አንቀጽ 14 ደግሞ በአሜሪካ የሚገኙ ነጻ የወጡ ባሪያዎችን የዜግነት መብት ጥያቄ የሚመልስ ሆነ።

በአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ክርክሮች ጥቁሮች የአሜሪካ ዜጋ መሆን እንደማይችሉ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ አንቀጽ 14 ለዚህ ክርክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ የሰጠ ነው።

አሜሪካ ውስጥ የተወለዱ የስደተኛ ልጆች ዜግነት ማግኘት አለማግኘትን በተመለከተ የአሜሪካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ውሳኔ ያስተላለፈው በ1898 ነበር።

ሰውዬው ዎንግ ኪም የሚባል የ24 ዓመት ወጣት ነው። ቤተሰቦቹ በስደት ወደ አሜሪካ መጥተው ነው እሱ የተወለደው።

የቤተሰቦቹን ሃገር ለመጎብኘት ወደ ቻይና ሄዶ ሲመለስ ግን የአሜሪካ ዜጋ አይደለህም ስለዚህ መግባት አትችልም ተብሎ ተከለከለ።

ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ወስዶ በክርክሩ አሸነፈ። ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ማንኛውም አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ሰው ቤተሰቦቹ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ይምጡ፣ ምንም አይነት የኑሮ ደረጃ ይኑራቸው የአሜሪካ ዜግነት ማግኘት እንደሚችሉ ተወሰነ።

ከዚህ ውሳኔም በኋላ የአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይህንን ጉዳይ በድጋሚ አይቶት አያውቅም።

3. በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በትራምፕ ውሳኔ ብቻ መቀየር ይቻላል?

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀጭን ትዕዛዝ የህገ መንግሥቱን አንድ ክፍል መቀየር አይችሉም። ሁሉም ነገር በህግና ደንብ መሰረት ስለሚሰራ በቀላሉ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው ብለዋል።

በቨርጂንያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፕሮፌሰርና የህገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት ሳይክሪሽና ፕራካሽ እንደሚሉት፤ "ይህ ሃሳብ ብዙ ሰዎችን የማያስደስትና በፍርድ ቤት ብቻ መወሰን የሚችል ነገር ነው። ፕሬዝዳንቱ ለብቻው መወሰን የሚችለው ነገር አይደለም።"

ባለሙያው ሲያብራሩ ፕሬዝዳንቱ ምናልባት የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ዜግነትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጠበቅ ያለ ህግ እንዲያወጡ ሊያዙ ይችላሉ፤ ነገር ግን ህጉን የማስቀየር ስልጣን የላቸውም።

ይሄ አካሄድ የማያባራ ክርክር የሚያስነሳ ሲሆን በመጨረሻ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለውሳኔ መቅረቡ አይቀርም።

"ነገር ግን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የአሜሪካ ዜግነት ከሌላቸው ወይም በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ ካልገቡ ሰዎች የሚወለዱ ልጆች ዜግነት ስለማግኘት አለማግኘታቸው ውሳኔ አላሳለፈም" ሲሉ 'በርዝራይት ሲቲዝንስ' መጽሃፍ ደራሲ ማርታ ጆንስ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረወዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

4. ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ምን አለ?

በመወለድ የሚገኝ የአሜሪካ ዜግነትን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየሰሩት ያለውን ነገር በቀጣይ ሳምንት ከሚካሄደው የአጋማሽ ወቅት ምርጫ ጋር አያይዞ መመለክት አስፈላጊ ነው።

መንግሥት ከ5ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ሜክሲኮ ድንበር ማሰማራቱና የፕሬዝዳንቱ ከዜግነት ጋር የተያያዘ አስተያየታቸው የአሜሪካዊያንን ትኩረት ወደ ኢሚግሬሽን ጉዳዮች ለማዞር ነው ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2016 የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ሲጀምሩም የኢሚግሬሽን ጉዳይ ዋናው ነጥባቸው የነበረ ሲሆን፤ ለማሸነፋቸውም እንደ ምክንያት ይጠቅሱታል።

5. ተመሳሳይ ህግ ያላቸው ሃገራት አሉ?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየታቸውን ሲሰጡ አሜሪካ በመወለድ የዜግነት መብት የምትሰጥ የዓለማችን ብቸኛዋ ሀገር ናት ብለው ነበር።

ነገር ግን ተሳስተዋል፤ የአሜሪካ ጎረቤት የሆኑት ካናዳና ሜክሲኮን ጨምሮ 33 የዓለማችን ሃገራት በሃገራቸው ለተወለዱ ህጻናት የዜግነት መብት ይሰጣሉ።

አብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገርም ሆነ የምሥራቅ እሲያ ሃገራት በመወለድ የዜግነት መብት የማይሰጡ ሲሆን፤ እንግሊዝ ግን ከቤተሰቦች መካከል አንዳቸው እንግሊዛዊ ከሆኑ አልያም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ካላቸው የዜግነት መብት ትሰጣለች።

6. ከዚህ ዜግነት መብት የሚጠቀመው ማነው?

ፒው የተባለው የምርምር ማዕከል በሰራው ጥናት መሰረት በአውሮፓውያኑ 2014 ዓ.ም ብቻ 275 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ከህገወጥ ስደተኞኛ ቤተሰቦች አሜሪካ ውስጥ ተወልደዋል።

በአውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ እና በ2000 አካባቢ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ከገቡ ቤተሰቦች ወይም ህጋዊ ወረቀት ከሌላቸው ቤተሰቦች የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እጅግ ጨምሯል።

በ2006 ከፍተኛ የሚባለውን ቁጥር አስመዘግቦ ከዚያ በኋላ ግን መቀነስ አሳይቷል።

ምንም እንኳን የምርምር ተቋሙ ስደተኞቹ ከየትኞቹ ሃገራት በብዛት ወደ አሜሪካ እንደሚገቡ ትክክለኛ ቁጥር ማግኘት ባይችልም፤ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ህገወጥ ስደተኞች ከላቲን አሜሪካ ሃገራት እንደሚመጡ ያስቀምታል።