ጠ/ሚ ዐብይ ጀርመን ውስጥ ባደረጉት ንግግር በፍትህ ተቋማት ላይ ለውጥ እንደሚደረግ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, DW/FB

በኢትዮጵያ የፍትህ ተቋማት ላይ መሰረታዊ ለውጥን የሚያመጡ ተከታታይ የለውጥ እርምጃዎች በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።

የፍትህ ዘርፉ በህዝቡ ዘንድ ገለልተኝነና ተአማኒነት እንዲኖረው የሚያስችሉት የማሻሻያ እርምጃዎች የፆታ ተዋጽኦንም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንደሚከናወን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ የተጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ውጤታማ እንደሚሆኑና ኢትዮጵያም ተለውጣ ለዜጎቿ የምትመች ታላቅ ሃገር እንደምትሆን ያላቸውን እምነትና ተስፋ "አምናለሁ! ተስፋም አደርጋለሁ!" ሲሉ በተደጋጋሚ በጎላ ድምፅ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በጀርመን ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፍራንክፈርት ውስጥ በአውሮፓ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር ነው ይህንን የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በንግግራቸው ላይ አስፈላጊ የሆኑት "የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ የምንመኘውን ፍትህ ሳይሆን ሥርዓት አልበኝነት እንጂ ፍትህ አይገኝም" ብለዋል።

ለዚህም በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግ አስፈላጊው ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም በአዲሱ የለውጥ እርምጃ ፍትህና ዲሞክራሲን ሊሸከሙና ሊያሰፍኑ የሚችሉ ተቋማት እየተገነቡ ከመሆናቸው ጎን ለጎን ብቁ ባለሙያዎችም እንደሚመደቡ ገልፀዋል።

ከፍትህ ሥርዓቱ በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ ነፃና ተአማኒ እንዲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እንደሚደረግበት፤ የደህንትና ፀጥታ ተቋማት ለውጥ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የመከላከያ ሠራዊቱም ዘመናዊና ሃገሪቱን የሚመጥን እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተስፋ የሚያጭሩና የሚያሳስቡ ሁኔታዎች እየተከሰቱ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ቢሆንም ግን "ኢትዮጵያን ማንም ተነስቶ እንደፈለገው የሚያደርጋት የግል ዕርስቱ ሳትሆን ዘመናት ያስቆጠረች ታላቅ ህዝብ የመሰረታት ታላቅ ሀገር ናት" በማለት ጠንክራ እንደምትወጣ ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ካለችበት ሁኔታ እንደትወጣ ሁሉም በኩሉን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበው፤ መንግሥታቸውም የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ተግቶ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

ለዚህም በውጪ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሃገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲገልፁ ጠይቀዋል። ጨምረውም ከዚህ በፊት በአሜሪካ እንዳደረጉት ኢትዮጵያዊያኑ በቀን አንድ ዶላር እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግር ባደረጉበት "በአንድነት እንነሳ፣ ነገንም እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ በኮሜርዝ ባንክ አሬና ስታዲየም በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከጀርመንና ከተለያዩ አውሮፓ ሃገራት ታድመዋል።