"ወንዶች በጡት ካንሠር እንደሚያዙ አላውቅም ነበር"

ሞሰስ ሙሶንጋ
የምስሉ መግለጫ,

ሞሰስ ሙሶንጋ እንደሚለው ህክምናው ከፍተኛ ህመም አለው

ሞሰስ ሙሶንጋ በሽታው እንዳለባቸው እስካወቁበት ጊዜ ድረስ የጡት ካንሰር ወንዶች ላይም እንደሚከሰት ፈጽሞ አያውቁም ነበር።

የ 67 ዓመቱ ኬንያዊ ለቢቢሲ እንደገለጹት በአውሮፓዊያኑ 2013 ደረጃ ሦስት የጡት ካንሰር እንዳለባቸው ዶክተሮች ሲነግሯቸው በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከመግባት ባለፈ ህይወታቸውንም እስከወዲያኛው ነበር የቀየረው።

"ወንዶችን የማያጠቃው እንዲህ ያለው በሽታ በዓለም ላይ ከሚገኙ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ወንዶች መካከል እኔን ላይ በመከሰቱ ሊሆን አይችልም በሚል ስሜት ውስጥ ከቶኝ ነበር" ይላሉ ሙሶንጋ።

መጀመሪያ ላይ በቀኝ ጡታቸው ጫፍ ላይ የተከሰተው እብጠት በየጊዜው ያድግ ነበር። ፈሳሽ መውጣት እና አለፍ ሲልም የደረት ህመም ተከተለ።

ስለጉዳዩ እርግጠኛ ባለመሆናቸው የአምስት ልጆች አባት ለሆኑት ሙሶንጋ ሐኪሞች የህመም ማስታገሻ ብቻ መስጠት ቀጠሉ። ጡቶቻቸው ከብዙ ወንዶች እጅግ በጣም የሚበልጡ ቢሆኑም ይህ ግን ለሙሶንጋ አስጨናቂ ነገር አልነበረም።

በቀኝ በኩል ያለው ጡት ቆዳው መቁሰል ሲጀምር ከፍተኛ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ሆነ። በተደረገው የናሙና ምርመራም ሙሶንጋ የጡት ካንሰር እንዳለባቸው ተረጋገጠ።

"የጡት ካንሰር ወንዶችን እንደሚያጠቃ ስለማላውቅ ጉዳት ያደረሰብኝ ነገር የጡት ካንሰር እንደነበር አላስተዋልኩም" ብለዋል።

በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ በሚገኘው የአጋ ካህን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አማካሪና የዕጢ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሲትና ምዋንዚ እንደሚሉት ወንዶች ላይ የሚያግጥመው የጡት ካንሰር የተለመደ አይደለም።

ከተሞክሮ እንዳወቁት ከ100 የጡት ካንሰር ህሙማን መካከል አንዱ ወንድ ነው።

ወንዶች ለምን በጡት ካንሠር ይያዛሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የወንዶች የጡት ካንሠር መነሻ ትክክለኛው ምክንያት ባይታወቅም በሚከተሉት ምክንያቶች የመከሰት ዕድሉ ሊጨምር ይችላል፡

  • የዘረ መል እና የቤተሰብ የጡት ካንሠር ታሪክ
  • በሰውነት ውስጥ የኤስትሮጅን መጠን ከፍ የሚያደርጉ ነገሮች። ከእነዚህ ውስጥ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት እና የጉበት ጠባሳ ይጠቀሳሉ።
  • ቀደም ሲል ደረት አካባቢ የተደረገ ራዲዮቴራፒ

ስጋትዎን ለመቀነስ ቢያደርጉ ሊረዳዎት ይችላል:

  • የተመጣጠነ ምግብ ይመገቡ
  • ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆኑ ክብደት መቀነሱ
  • ከመጠን በላይ አልኮል ከመጠጣት ይቆጠቡ

ምንጭ: የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት

የዓለም የጤና ድርጅት የምርምር አካል የሆነው ግሎቦካን 2008 እንዳለው በመላው አፍሪካ 170,000 ያህል ህሙማን እንዳሉ ይገመታል።

ዶክተር ምዋንዚ እንደሚሉት ከወንዶች የበለጠ ተፈጥሮአዊ ኦስትሮጀን ያላቸው መሆኑን ጨምሮ ሴቶች በተለያየ ምክንያት ለችግሩ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

"ኤስትሮጅን በብዛት ካለ ተጨማሪ የጡት ህብረ ህዋሳትን የሚፈጥር ሲሆን አንዳንዴ እነዚህ ያልተለመደ እድገት ከመፍጠር ባለፈ ወደ የጡት ካንሠር ሊያመሩ ይችላሉ" ብለዋል።

ዶክተር ምዋንዚ አክለው እንደተናገሩት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በተለይም በጡት ላይ እብጠትን ጨምሮ ሌሎች ምልክቶችን ሊከታተሉ ይገባል።

በጡት እና በጡቱ ላይ ያለው የቆዳ ለውጥ፤ ከጡቱ የሚወጣ በደም የተሞላ ፈሳሽ እና የአንዱ ወይም የሁለቱም ጡቶች ቅርፅ ወይም መጠን ለውጥ ሌሎቹ ምልክቶች ናቸው።

ካንሠር የክብደት መቀነስ ሊያመጣ ይችላል።

ዶክተር ምዋንዚ እንደሚሉት የጡት ካንሠር ዋና ሕክምናዎች ራዲያቴራፒ፣ ኬሞቴራፒ፣ ቀዶ ህክምና እና የሆርሞን ሕክምናዎች ናቸው።

"ወንዶች የጡቶቻቸውን ጫፍ ማየት አለባቸው። ራሳቸውን በየጊዜው መፈተሽም አለባቸው" ብለዋል።

"ምንም መድልዎ የለም"

የ67 ዓመቱ ኬንያዊ የኬሞቴራፒ ሕክምናቸውን ከጀመሩ በኋላ በመተንፈስ ችግር ምክንያት በኮሌጅ ማስተማራቸውን ለማቆም ተገደዋል።

የጡት ካንሰር ከሴቶች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሙሶንጋ ስለህክምናው ለሰዎች በሚነግሩበት ወቅት መድሎዎ እንዳይደርስባቸው ይፈሩ ነበር።

"ብዙ ሰዎች ከመደንገጥ እና ከመፍረድ ይልቅ በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት አድርገው ስለሚያስቡት የጡት ካንሰር የበለጠ ለማወቅ ይፈልጋሉ " ብለዋል።

በሽታውን በቁም ነገር እንዲወስዱና ህክምና ቶሎ እንዲጀምሩ ወንዶችን ይመክራሉ። "ሊቀበሉት ይገባል። ሊታከሙ እና ወደ የተለመደ ህይወታቸው ሊመለሱ ይችላሉ" ብለዋል።