ቱርክ የሳዑዲ አረቢያው ጋዜጠኛ ግድያን መረጃ ይፋ አደረገች

Jamal Khashoggi pictured in 2004

የፎቶው ባለመብት, PA

ቱርክ በሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛው ጃማል ካሾግጂ ግድያ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦፊሴሊያዊ መረጃ ይፋ አድርጋለች።

ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ አራቢያ ቆንስላ ውስጥ እንደተገደለ የታመነው ካሾግጂ ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባ ነበር የታነቀው ስትል ቱርክ መግለጫ ሰጥታለች።

ለሳምንታት የዓለም መገናኛ ብዙሃን ወሬ ማሟሻ ሆኖ የሰነበተው የካሾግጂ ግድያ ጉዳይ ቱርክ መረጃ እስክታወጣ ድረስ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።

ምንም እንኳ ቱርክ ለመረጃዋ ማስረጃ ማቅረብ ግድ ቢላትም «በታቀደው መሠረት ካሾግጂ ልክ ወደ ቆንፅላው ቅጥር ግቢ ሲገባ በገዳዮች ታንቆ ነው የተገደለው» ስትል አትታለች።

ከዚያም ይላል መረጃው ሲቀጥል «ከዚያም የጋዜጠኛው በድን አካል ተቆራርጦ እንዲጠፋ ተደርጓል። ይሁ ሁሉ የተከናወነው ቀድሞ በተፃፈ ስክሪፕት መሠረት ነው።»

የቱርኩ ዋና አቃቤ ሕግ ኢርፋን ፊዳን ከሳዑዲ አቻቸው ጋር የነበራቸው ውይይት ውጤት አልባ እንደበረ ተነግሯል፤ ምንም እንኳ ሳዑዲ ስለጉዳዩ ሹክ ያለችው አንድም ነገር የለም።

መኖሪያውን አሜሪካ በማድረግ ለዋሽንግተን ፖስት ይፅፍ የነበረው ሳዑዲ አረቢያዊው ካሾግጂ የንጉስ ሞሓመድ ቢን ሰልማን ቀንደኛ ተቺ እንደነበር ይነግርለታል።

ምንም እንኳ የሰውዬው ሬሳ የት ይግባ የት ባይታወቅም ቱርክ፣ ሳዑዲ እንዲሁም አሜሪካ ካሾግጂ የሳዑዲ ቆንፅላ ፅ/ቤት ውስጥ እንደተገደለ እሙን ነው ብለዋል።

በአሟሟቱ ላይ ግን የተለያየ መረጃ የምትሰጠውን ሳዑዲን ጨምሮ ሶስቱም ሃገራት ሰምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።

ቱርክ መገናኛ ብዙሃን በካሾግጂ ጉዳይ ከታማኝ ምንⶐች ያገኘናቸው ያሏቸውን ዝርዘር መረጃዎች ከማውጣት አልቦዘኑም።